
አዲስ አበባ: ሐምሌ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ኢትዮጵያ በሠራችው የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ሥራ በኢትዮጵያ የሚገኙ ኢምባሲዎች በሙሉ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተሳትፈው ችግኝ ተክለዋል ብለዋል። በውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቆንጽላዎችም ተክልዋል ተብሏል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ የተመራ የልዑካን ቡድን በሀረሪ እና ድሬዳዋ አረንጓዴ አሻራ ላይ መሳተፉንም አንስተዋል። ባለፈው ዓመት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላይ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮጀክት ሒደት እና ስኬታማነት መነሳቱን አስታወሰው የአረንጓዴ አሻራ የገንዘብ ምንጭ በማፈላለግ ለመደገፍ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊነቱን ይወጣል ብለዋል።
በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሔደው የአፍሪካ ኀብረት የአስፈጻሚዎች ጉባኤ በኬንያ ናይሮቢ የተደረገው ስብሰባ ስኬታማ እንደነበር ያነሱት አምባሳደሩ በጉባኤው ኢትዮጵያ ከግጭት ወደ ሰላም የሄደችበት መንገድ ለአፍሪካ ምሳሌ ተደርጎ መወሰድ እንዳለበት ጉባኤው ውይይት አድርጓል ብለዋል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮነን የተመራው ልዑክ በጉባኤው መሳተፉን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ለጉባኤው ያቀረባቻቸው ሐሳቦችም ተቀባይነት አግኝተዋል ነው ያሉት፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ከኬንያ፣ ከሶማሊያ፣ ኮትዲቯር ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከማሊ፣ ቻድ፣ ሞሮኮ እና ናይጀሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
የአፍሪካ ኀብረት ዓመታዊ በጀት 605 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መጽደቁን ያስታወሱት አምባሳደር መለስ ይህን በጀት በአግባቡ መጠቀም አንደሚገባ ጉባኤው ውሳኔ አሳልፏል ብለዋል። በሚቀጥለው የተመድ ስብሰባ ላይ 4 ኢትዮጵያውያን በተቋሙ የኀላፊነት ቦታዎች ገብተው እንዲሠሩ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድጋፍ እያደረገ ሲኾን በአፍሪካ ኀብረት ውስጥም በዚህ አካሔድ አንድ ሰው በተቋሙ ኃላፊነት ቦታ ማስመረጥ ተችሏል ብለዋል።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!