
ባሕር ዳር: ሐምሌ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በማሽን እና በኅብረተሰብ ተሳትፎ 1 ሺህ 600 ሄክታር መሬት ላይ የእምቦጭ አረም መወገዱን ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በምክር ቤት ጉባዔ ላይ አንስተዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ በአካባቢ እና ብዝሀ ሕይወት ሃብት ላይ መጤ፣ ተስፋፊና ወራሪ የአረም ዝርያዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ነው ብለዋል። እነዚህ አረሞች በሥነ ምህዳር ላይ መዛባትን የሚያስከትሉ ሲኾን የአፈርን ጤና በማወክ በምርትና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ ናቸው ብለዋል።
ከመጤ አረሞች መካከል አንዱ የኾነውና በጣና ሐይቅ ላይ ተስፋፍቶ የሚገኘውን የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ በበጀት ዓመቱ ርብርብ ሲደረግ መቆየቱን ርእሰ መሥተዳድሩ አንስተዋል። ባለፋት 11 ወራት በኅብረተሰብ ተሳትፎ እና በማሽን በመታገዝ 1 ሺህ 600 ሄክታር መሬት ላይ እምቦጭ አረም መወገዱንም ተናግረዋል።
እንቦጭን ጨምሮ ሌሎችንም መጤ አረሞችን በመቆጣጠር አካባቢያዊ ተጽዕኖዎችን ለመከላከል ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሠራት እንዳለበትም ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!