
ባሕር ዳር: ሐምሌ 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ከሐምሌ 12 እስከ 14/2015 ዓ.ም የሚካሄደውን 6ኛ ዙር፣ 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 6ኛ መደበኛ ጉባዔውን ጀምሯል።
በጉባዔው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የተከበሩ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋየ በበጀት ዓመቱ በክልሉ የተያዙ የልማት ሥራዎች አፈጻጸም የሚያበረታታ ነበር ብለዋል። የክልላችንን ብሎም የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ በስንዴ ልማት፣ በእርሻ ሜካናይዜሽን እንዲሁም በአረንጓዴ አሻራ እና በትምህርቱ ዘርፍ በከፍተኛ ንቅናቄ የተሠራበት ዓመት እንደነበርም ገልጸዋል።
የማዳበሪያ እጥረት የወለደው የሕገወጦች መበራከት በክልሉ አርሶ አደሮች በኩል ቅሬታን የፈጠረ መኾኑን የገለጹት አፈ ጉባዔዋ ለጉዳዩ ዘላቂ እልባት ለመስጠት የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
አፈ ጉባዔዋ “የክልሉ ሕዝብ የመጀመሪያ ጥያቄ ልማት እና የሕግ የበላይነት መከበር ነው” ሲሉ ገልጸዋል። መንግሥት የመሪነቱን ተግባር በትክክል በመወጣት የሕዝቡን ጥያቄ ፈጥኖ መመለስ አለበት ሲሉም ተናግረዋል። በተለይም ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት በመኾኑ መላ የክልሉ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን በመቆም ሰላሙን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ምክር ቤቱ በሦስት የጉባዔ ቀናት ልዩ ልዩ ተግባራትን የሚያከናውን ሲኾን ከነዚህም መካከል:-
👉 የመደበኛ ጉባዔውን አጀንዳዎች እና ቃለ ጉባዔ መርምሮ ማጽደቅ
👉 የክልሉን አስፈጻሚ አካላት የ2015 በጀት ዓመት የ11 ወር እቅድ አፈጻጸም የተጠቃለለ ሪፖርት መርምሮ ማጽደቅ
👉 የክልሉን ፍርድ ቤቶችን የ2015 በጀት ዓመት የ11 ወር እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት መርምሮ ማጽደቅ
👉የአማራ ክልል የ2016 በጀት ዓመት ጥቅል የበጀት ጣሪያ አመዳደብ እና የወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች የድጎማ በጀት ቀመር እና የ2016 በጀትን ለማጽደቅ የበጀት አስተዳደሩን ለመወሰን የወጣ አዋጅን መርምሮ ማጽደቅ
👉 የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የ2016 በጀት ዓመት በጀትን መርምሮ ማጽደቅ
👉 የክልሉን ኦዲት መሥሪያ ቤት የ2016 በጀት ዓመት በጀቱን መርምሮ ያጸድቃል
👉የምክር ቤቱን የ2016 በጀት ዓመት በጀቱን መርምሮ ማጽደቅ እና
👉 ልዩ ልዩ ሹመቶችን መርምሮ ማጽደቅ በአጀንዳነት ተይዘዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!