“አልሚ ባለሃብቶችን በመደገፍ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እየተሠራ ነው” የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ

51

ባሕር ዳር: ሐምሌ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት በባሕርዳር ከተማ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል። አባላቱ በዋናነት ከተመለከቷቸው የልማት ሥራዎች መካከል አባይ የምግብ ዘይት ፋብሪካ፣ ራቫል ብረታ ብረት ፋብሪካ እና ገደፋው ይስማው አውቶሞቲቭ ትሬለር ማኑፋክቸሪንግ ይገኙበታል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋየ የምልከታው ዋና ዓላማ በክልላችን ውስጥ የሚከናወነውን አጠቃላይ የልማት ሥራ ሚዛናዊ በኾነ መልኩ ለመገንዘብ እና ለመረጠን ሕዝብም ለማስረዳት ነው ብለዋል። ምልከታው ለልማት እንቅፋት የኾኑ ጉዳዮችን ለይቶ በምክር ቤቱ ለመምከር እና ለአስፈጻሚው አካል አስፈላጊውን ክትትል እና ድጋፍ ለማድረግም ያግዛል ነው ያሉት። አፈ ጉባዔዋ ባሕርዳርን ጨምሮ በሌሎችም የክልሉ ከተሞች በባለሃብቶች የሚንቀሳቀሱ በርካታ ኢንዱስትሪዎች እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

የምክር ቤት አባላት በየአካባቢያቸው ያሉ አልሚ ባለሃብቶች በሙሉ አቅም እንዲሠሩ ለማስቻል ከአስፈጻሚ አካላት ጋር በመተሳሰር መደገፍ እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል። የክልሉ ምክር ቤት በባለሃብቶች የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት የሚኾኑ ጉዳዮችን ለይቶ በመፍታት አስፈላጊውን ሁሉ እገዛ እንደሚያደርግም ተናግረዋል። ምልከታ ከተካሄደባቸው ፋብሪካዎች መካከል አንዱ የኾነው የዓባይ የምግብ ዘይት ፋብሪካ ባለቤት አቶ የሻንበል መንገሻ ፋብሪካው የተለያዩ ሰብሎችን በመጠቀም በቀን እስከ አንድ ሚሊዮን ሊትር ዘይት ያመርታል ብለዋል። ለዚህም ሶስት ሺህ ኩንታል የቅባት እህሎችን ይጠቀማል ነው ያሉት። ፋብሪካው ተረፈ ምርቱን በመጠቀም 2 ሺህ 400 ኩንታል የእንስሳት መኖ እያመረተ እንደሚገኝ አቶ የሻንበል ተናግረዋል። የመብራት መቆራረጥ ችግር ፋብሪካው በሙሉ አቅም እንዳያመርት አድርጎታል ያሉት አቶ የሻንበል ችግሩ መቀረፍ እንዳለበትም አሳስበዋል

ሌላው የጉብኝቱ አካል የነበረው የገደፋው ይስማው አውቶሞቲቭ ትሬለር ማኑፋክቸሪንግ ባለቤት አቶ ገደፋው ይስማው የተሳቢ መኪና አካል ሥራ ከዚህ በፊት በአማራ ክልል እንዳልነበረ ነግረውናል። ፋብሪካው ከተሳቢ ተሽከርካሪ በተጨማሪ የነዳጅ ቦቴዎችን እና ለነዳጅ ማደያዎች የሚያገለግል ታንከር እየሠራ ነው። አቶ ገደፋው የሥራ ቦታ ማስፋፊያ ተፈቅዶላቸው እየሠሩ ስለመኾኑ ገልጸው እንደሀገር የገጠመው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ እንዳይሠራ እንቅፋት ስለመኾኑ ገልጸዋል። ፋብሪካው በዓመት ከ200 በላይ ተሳቢ መኪናዎችን የመሥራት አቅም ቢኖረውም አሁን ላይ 50 መኪኖችን እንደሚሠራ ተናግረዋል።

ሌላው ምልከታ የተካሄደበት የራቫል ብረታ ብረት ፋብሪካ የሰው ሃብት አሥተዳደር እና መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ መንግሥቱ አርቄ ለምክር ቤቱ አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል። ፋብሪካው የወዳደቁ የብረት ቁርጥራጮችን በመጠቀም ፌሮ፣ አንጉላሬ እና ቱቦላሬ የተባሉ የብረት አይነቶችን በማምረት ለገበያ እያቀረበ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ለ700 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩንም አቶ መንግሥቱ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ “አልሚ ባለሃብቶችን በመደገፍ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እየተሠራ ነው” ሲሉ በምልከታው ላይ ተናግረዋል። የሚገጥሙ ፈተናዎችን እየተቋቋሙ ውጤታማ የኾኑ በርካታ አልሚ ባለሃብቶች በአማራ ክልል እንደሚገኙም አንስተዋል። የእነዚህን ባለሃብቶች የልማት ተግዳሮቶች ተረባርቦ በመፍታት በሙሉ አቅማቸው ወደ ልማት እንዲገቡ እና የሥራ እድል እንዲፈጥሩ በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑም ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

Previous article“በአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ ያስመዘገብነው ታሪካዊ ድል በሌሎችም የግብርና ሥራዎች ተጠናክሮ ይቀጥላል” ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ.ር)
Next articleየአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር መደበኛ ጉባዔውን ጀመረ።