“በአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ ያስመዘገብነው ታሪካዊ ድል በሌሎችም የግብርና ሥራዎች ተጠናክሮ ይቀጥላል” ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ.ር)

63

ባሕር ዳር: ሐምሌ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ.ር) ለቀጣይ የግብርና ሥራዎች ሥኬታማነት መልእክት አስተላልፈዋል።
ሙሉ መልእክቱ ቀጥሎ ቀርቧል፦

ውድ የግብርና ቤተሰቦች በትናንትናው እለት በአንድ ጀንበር 260 ሚሊዮን ችግኝ እንተክላለን ብለን አቅደን ከ278 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ተክለናል። አሳክተነዋል። እንኳን ደስ አለን እንኳን ደስ አላችሁ።በዚህ ታሪካዊ ቀን የተሳተፋችሁ መላ የክልላችን ሕዝብ በራሴና በግብርና ቢሮ ስም ከፍ ያለ ምስጋየንም አቀርባለሁ። በአንድ ቀን በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ አደራጅቶ ለልማት ማሰማራት እና ከእቅድ በላይ የመፈፀም ምክንያት ሌላ ሚስጥር የለውም።

ጠንካራ የቅድመ ዝግጅት ሥራ በመሠራቱ፣ ድጋፍ፣ ክትትልና ግብረ መልስ ወዲያው የተግባር ስምሪት በመኖሩ እና ከሁሉም በላይ በአመራሩ፣በግብርና በባለሙያዎች እና በመላ ሕዝባችን እናሳካዋለን የሚል ቁርጠኝነት በመኖሩ ነው። የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። የተከልነውን ችግኝ የመንከባከብ ኃላፊነታችንን እንወጣ። በአንድ ጀንበር አንድን ተግባር ለአንድ አላማ በአንድነት ተሰልፎ የመፈፀም ልምምድ አዳብረናል። ይህ ልምምድ በሌሎች የክረምት የግብርና ሥራዎች ተጠናክሮ ይቀጥላል ።

በ2015/16 ምርት ዘመን 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 160 ሚሊዮን ኩንታል ለማግኘት ከፍተኛ እርብርብ እያደረግን እንገኛለን። ስኬቶቻችንን አፅንተን፣ ፈተናዎችን እየተሻገርን ዛሬም እንደትናንቱ በከፍተኛ ትጋትና ቁርጠኝነት እንድንሰራ ጥሪ አቀርባለሁ።

ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ.ር)
የአብክመ ግብርና ቢሮ ኃላፊ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ለአዲሱ የሰሜን ጎጃም ዞን አሥተዳድር አመራሮች ሹመት ሰጡ።
Next article“አልሚ ባለሃብቶችን በመደገፍ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እየተሠራ ነው” የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ