
ባሕር ዳር: ሐምሌ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) እ.ኤ.አ በ2015/16 በተሠራ ጥናት በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለጤና አገልግሎት በሚያወጡት ወጪ ምክንያት ወደ ድህነት አረንቋ ይገባሉ።
በኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት እና በጤና ሚኒስቴር አዘጋጅነት በማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አፈጻጸም እና በቀጣይ ዕቅድ ላይ በሳይንስ ሙዚየም የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት የክልል ቅርንጫፍ ኀላፊዎች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ዋና ዳይሬክተር ፍሬሕይወት አበበ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በተደረገ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት አጠቃቀም የግንዛቤ ሥራ ከ56 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የአገልግሎቱ አባል ማድረግ ተችሏል።
ወይዘሮ ፍሬሕይወት በማኅበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት ትግበራ ሂደት የተስተዋሉ እና ወደፊት ሰፊ ሥራ የሚያስፈልጋቸው ተግዳሮቶች ብለው ከጠቀሷቸው ውስጥ:-
✍️የጤና አገልግሎት ጥራት መጓደል እና የአቅርቦት ችግር
✍️ገቢን መሠረት ያላደረገ ተመሳሳይ የመዋጮ መጠን መኖር
✍️ያልዘመነ እና ቴክኖሎጂን ማዕከል ያላደረገ ትግበራ
✍️የአጋር አካላት ድጋፍ መቀነስና ከነጭራሹ መጥፋት ይገኙበታል
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት፡-
👉የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ ማዘጋጀት
👉አሠራርን ማዘመን
👉የአጋር አካላትን የድጋፍ ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሯ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!