“ዳያስፖራው በሀገራዊ የልማት ሂደት ውስጥ እያበረከተ ያለውን በጎ አስተዋጽዖ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል” አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

55

ባሕር ዳር: ሐምሌ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ)ዳያስፖራው በሀገራዊ የልማት ሂደት ውስጥ እያበረከታቸው ያሉ በጎ አስተዋጽኦችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።

በሰሜን አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ ከሚኖሩ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት ጋር ዘላቂ ሀገራዊ ትስስርና ተሳትፎን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተካሄዷል።

በውይይቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ እና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ እና የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ ዳያስፖራው ለሀገሩ ጥብቅና በመቆምና ድጋፍ በመስጠት፣ የሀገር ድምጽ በመሆንና ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አሻራውን በማስቀመጥ ላደረገው አበርክቶ ምስጋና አቅርበው ጥረቱን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

ዳያስፖራው ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ነጻነት በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ እንዲሁም በቢዝነስ እድሎች ላይ በስፋት መሳተፍ ይጠበቅበታል ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ በበኩላቸው ዳያስፖራው የአገሩ አምባሳደር በመሆን በገጽታ ግንባታ፣ በኢኮኖሚ፣ በባሕልና በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ያደረገው አስተዋጽዖ ዘመን ተሻጋሪ ነው ብለዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘላቂ ሀገራዊ ትስስርና ተሳትፎን ለማጠናከር በአዳዲስ እሳቤዎች መምራት እንደሚያስፈልግ ገልጸው ተቋሙ ለቀጣይ ጊዜ የሚሆኑ አዳዲስ አስተሳሰቦችን፣ አሰራሮችንና ፓኬጆችን ለመተግበር መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ዳያስፖራው በሀገራዊ ልማት፣ በገጽታ ግንባታ፣ በዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ተሳትፎውን ማሳደግ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ሀገራዊና ወቅታዊ አጀንዳዎችን፣ የመረጃ ተደራሽነት፣ በኢንቨስትመንት ተሳትፎ ላይ የሚያጋጥሙ እንቅፋቶች፣ የዳያስፖራ መብቶች፣ የአገልግሎት አሰጣጥንና ተያያዥ ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥያቄና ሀሳቦችን አቅርበው ምላሽና ማብራሪያ መሰጠቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

እንደ አገር ያጋጠሙትን ፈተናዎች በውይይትና በመመካከር መፍታት እንዲቻል ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን፣ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱንና የመልሶ ግንባታ ሥራዎችን ዳያስፖራው መከታተል፣ ማወቅና መደገፍ እንደሚገባው ተገልጿል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ 75 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ትርፍ አገኘ።
Next articleበኩር ጋዜጣ በሐምሌ 10/2015 ዓ.ም ዕትሟ