
ባሕር ዳር: ሐምሌ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር በላይነህ አድማሱ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ የግንባታ ቦታዎች ከሥራ ላይ አደጋና ጤንነት ስጋት ነፃ ሊሆኑ ይገባል። የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ለሀገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ቢኖረውም የሥራ ላይ ደህንነት፣ ጤና እና የአካባቢ ደህንነት ሁኔታን በቀጥታ የሚመለከት የሕግ ማዕቀፍ የለውም።
ጉዳቱ እና አደጋው እያለ የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ በርካታ ሰዎች የሚገባቸውን ካሳ እያገኙ አይደለም ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የግንባታ ቦታ ደህንነት እና ጤና ደንብ፣ የሕግ ማዕቀፍና የትግበራ መመሪያ እንዲዘጋጅ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የግንባታ ሠራተኞች በሥራ ላይ ለሚደርስባቸው አደጋ የመድህን ሽፋን እንዲያገኙ የሚያስችል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ምክክር እየተደረገበት ነው ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ ደንቡን ማዘጋጀት ያስፈለገበት ምክንያት በሀገሪቱ የግንባታ ሠራተኞች ላይ ከፍተኛ አደጋ እየደረሰ መሆኑ በጥናት በመረጋገጡ እንደሆነ ገልጸዋል።
እንደተባባሪ ፕሮፌሰሩ ገለፃ፤ በደንቡ የሠራተኞችን ደህንነት፣ ጤንነት፣ የአካባቢ ጥበቃና መድህንን የሚመለከት ጽንሰ ሃሳቦች ተካተዋል። ደንቡ 17 ክፍሎችን የያዘ ሲሆን በዋናነት የሠራተኛውን ደህንነት፣ ጤንነት እና ማኅበራዊ ጥበቃን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ይዟል። ይህም የሠራተኛውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካላዊ እንዲሁም አዕምሯዊ ደህንነት ይጠብቃል።
ደንቡ ይህንን ማስከበር የሚችል 102 አንቀጾች እንዳሉት ጠቅሰው፤ የተለያዩ መመሪያዎችን ወደ ተግባር እንዲወርዱ ለማድረግ ረቂቅ ደንቡ ለምክር ቤቶች እንዲቀርብ እየተሠራ ነው። ይህም የሠራተኞች ደህንነት እና ካሳ እንዲሁም የመድህን ሽፋን እንዲያገኙ በማድረግ ጠንቃቃ እና አምራች ትውልድ ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ላይ የተሳለጠ የአሠራር ሥርዓት እንዲሰፍን፤ የኮንስትራክሽን ሠራተኞች የሥራ ላይ ደህንነት፣ ጤናና አካባቢን ያማከለ የቁጥጥር የሕግ ማዕቀፎችን እንዲሁም ኢንዱስትሪውን በውጤታማነት ለመምራት እና ለማስተዳደር የሚያስችሉ ሥራዎችን ሊሠራ እንደሚገባም አስረድተዋል።
አሠሪዎች፣ ተቋራጮችና አማካሪዎች ግንባታ ከማከናወን በተጨማሪ የሠራተኛውን ደህንነትና ጤንነት የመጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ አሰሪ መሥሪያ ቤቶች ፕሮጀክታቸውን በሚቀርፁበት ወቅት የግንባታ ቦታ ደህንነት እና ጤና ደንብ፣ የሕግ ማዕቀፍ እና የትግበራ መመሪያ መዘርጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ሠራተኞችም ተገቢውን ሥልጠና በመውሰድ ራሳቸውን ከአደጋ ሊጠብቁ ይገባል። በዚህ ሂደት ባለድርሻ አካላት የራሳቸውን ሚና በመወጣት በሥራ ቦታና በአካባቢ ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን በመቀነስ የዘርፉን በጎ ሚና ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!