“ስንተባበር የማንመክተው ችግር በድል የማንወጣው ፈተና የለም” የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ግዛቸው ሙሉነህ

40

ባሕር ዳር: ሐምሌ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተያዘውን ዕቅድ ከቀኑ 10 ሰዓት በፊት በማጠናቀቅ በድል ተወጥተናል ሲሉ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ገልጸዋል።

መላው የክልሉ ሕዝብ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሚሰጠውን የምጣኔ ሃብት፣ የሥነ ምህዳር፣ የኢኮ ቱሪዝም እና ዘርፈ ብዙ የልማት ጠቀሜታዎች በመረዳት ላደረገው ርብርብ በክልሉ መንግሥት ስም የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ምስጋና እናቀርባለን ብለዋል።

የአማራ ክልል የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እንደየካባቢው የአየር ንብረት ሁኔታ እስከ መስከረም መጨረሻ ገደማ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሥራው የሚቀጥል መሆኑን በመረዳት አሁንም ለቀሪ ሥራዎች ርብርብ እንዲደረግ ከወዲሁ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በዚህ የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንደታየው ስንተባበርና ስንደመር የማንፈጽመው ዕቅድ ፤ የማንወጣውም ችግር የለም ነው ያሉት።

ስለሆነም በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተገኘው ድል በቀሪ የግብርና ሥራዎች፣ በዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በሁሉም መንግሥታዊ አፈጻጸሞች ቀዳሚ ባለ ድል ኾኖ ለመገኘት አሁንም መረባረብ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

“ለመላው የክልላችን ሕዝብ በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለፈጸማችሁት ስኬት እና ለነበራችሁ ልባዊ ተሳትፎና ቁርጠኝነት ምስጋናችን ይድረሳችሁ ፤ ስንተባበር የማንመክተው ችግር በድል የማንወጣው ፈተና የለም” ነው ያሉት አቶ ግዛቸው። መረጃው የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በሁሉም የክልላችን አካባቢ ያከናወነው የአንድ ጀንበር አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በስኬት ተጠናቋል” ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ
Next articleየግንባታ ሠራተኞች በሥራ ላይ ለሚደርስባቸው አደጋ የመድህን ሽፋን እንዲያገኙ የሚያስችል ረቂቅ ደንብ መዘጋጀቱ ተገለጸ።