
ባሕር ዳር: ሐምሌ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በክልሉ የ500 ሚሊዮን የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር በስኬት መጠናቀቅን አስመልክቶ መልእክት አስተላልፈዋል። በመልእክታቸው የመልማት ትልቁ አቅማችን አንድነታችንና ትብብራችን ነው ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ስኬትም ከተባበሩ ለድል እንደሚበቃ ታላቅ ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።
“አንድ ከሆን የማንፈታው ችግር የለም። አንድነታችንና ትብብራችንን በዘላቂነት ማጽናት አለብን” ነው ያሉት።
በጋራ ጥረታችን ዛሬ የተከልነው ችግኝ ለመጭው ትውልድ የምናስረክበው የጋራ ሃብት ነው። ቅርስና ጌጥም ነው። የችግኝ ተከላ የአንድ ወቅት ተግባር ብቻ ሳይሆን ባሕል ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ተከላውን ማከናወን ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ ለቁም ነገር ማብቃት ከሁላችንም የሚጠበቅ ኃላፊነት እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡
የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በቀጣይ የክረምት ወራትም የሁላችንም የቤት ሥራ ሆኖ መቀጠል ይኖርበታል። የአንድ ጀንበር ድሉን በክረምት እቅዳችን ለመድገም ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ሁሉም አካል ከክልሉ መንግሥት ጎን በመሆን የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክትም አሳስበዋል።
ለአንድ ጀንበር አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ እቅድ ስኬታማነት አሻራችሁን በማሳረፍ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ላበረከታችሁ ሁሉ በራሴና በክልሉ መንግሥት ስም ከፍ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ።
መረጃው የርእሰ መስተዳደር ጽሕፈት ቤት ነው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
