
ባሕር ዳር: ሐምሌ 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “500 ሚልዮን ዛፎችን በመትከል የራሳችንን ሪከርድ እንድንሰብር የቀረበውን ጥሪ ተቀብላችሁ የወጣችሁ ሁሉ ምስጋና ይገባችኋል። አረንጓዴ ታሪክ ሠርታችኋል። አረንጓዴ ታሪክ ጽፋችኋል” ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
የተዛባ አየር፣ የተራቆተ ምድር ለትውልድ አናወርስም በሚል ፤ ጎሕ ሳይቀድ ወደ ተራሮችና ሸለቆዎች፣ ወደ ሜዳዎችና ሸንተረሮች ተሠማርታችሁ 566 ሚልዮን ዛፎች ተክላችኋል። ሪከርዳችሁን ሰብራችኋል ለዚህም ምስጋና ይገባቹሃል ብለዋል።
በሁሉም ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ዛፎች ተተክለዋል። ከ9 ሺ በላይ የተለዩ ቦታዎች ተዘጋጅተው ነበር። ከ3600 በላይ የሚዲያ ባለሞያዎች በመላ ሀገሪቱ ተሠማርተው ነበር። የቴሌና የግብርና ባለሞያዎች የመረጃ አያያዙ ዘመናዊ እንዲሆን ሠርተዋል። የአዲስ አበባ ታክሲዎች ነጻ ትራንስፖርት ለችግኝ ተካዮች መስጠታቸውንም ገልጸዋል። ሕጻናት፣ እናቶች፣ አባቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ በነቂስ ወጥተው ተክለዋል፤ በኢትዮጵያውያን አረንጓዴ ታሪክ ተሠርቷል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ከተባበርን የማንሰብረው ሪከርድ የለም ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትሩ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
