“የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይኾን ዘወትር ተንከባክቦ ማሳደግን ባሕልና ልምድ ልናደርግ ይገባል” የሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ

42

ወልደያ: ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሁለተኛው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በሰሜን ወሎ ዞን ዋድላ ወረዳ እየተካሄደ ነው፡፡ በዞኑ የ2015 ዓ.ም በአንድ ጀምበር አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር 21 ሚሊዮን ችግኞች በዋድላ ወረዳ መለይ 017 ቀበሌ ስጋ ማረጃ ተፋሰስ እየተተከለ ነው።

የዞኑ የግብርና መምሪያ ኀላፊ አቶ ተገኘ አባተ እንዲሁም ሌሎች የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት ችግኝ ተከላው ተካሂዷል፡፡
በሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አቶ ተገኘ አባተ

በችግኝ ተከላው እንዳሉት ኢትዮጵያ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ እየሠራች ነው፡፡ እኛም የዞናችንና የአካባቢያችንን የደን ብዝኃ ሕይወት ለመመለስ ችግኝ መትከል ለምርጫ የምናቀርበው ጉዳይ አይደለም ብለዋል።
የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይኾን ዘወትር ተንከባክቦ ማሳደግን ባሕልና ልምድ ልናደርግ ይገባል” ያሉት ኀላፊው በየዓመቱ የሚተከሉ ችግኞች ለሚፈለገው ውጤት ማብቃትና ማድረስ ይጠበቅብናል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ባለፈው ዓመት በዞኑ በተሠራው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር 67 በመቶ መጽደቁን አስታውሰው ዘንድሮ የታቀደውን 124 ሚሊዮን በላይ የደንና ከ800 ሺህ ያላነሰ የቡናና አትክልት ችግኞችን በመትከል በዞኑ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አማካሪ አቶ ማርቆስ ወንዴ መገኘታቸውን የዘገበው የሰሜን ወሎ ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ነው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሀገር አቀፍ ደረጃ እስከ አሁን 372 ሚሊየን ችግኞች ተተክለዋል።
Next article“የአረንጓዴ አሻራን መርሐ ግብርን የሕልውና ጉዳይ አድርገን ማየት አለብን” ርእሰ መሥተዳደር ሙስጠፌ ሙሐመድ