
በደሴ ከተማ የሚገኙ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ አባላት በእምነት ተቋማት ላይ የደረሰውን ጥቃት አወገዙ፡፡
በደሴ ከተማ አስተዳደር ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ ክፍሎች የተወጣጡ የእምነቱ ተከታዮች በሞጣ ከተማ በእምነት ተቋማት ላይ ደረሰው ጥቃት አሳፋሪ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የእምነቱ ተከታዮች በደሴ ከተማ በሚገኘው ዐረብ ገንዳ መስጂድ ባደረጉት ውይይት አጥፊዎቹ በሕግ ሊጠየቁ እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡
ጥቃቱ ከመድረሱ በፊትም ሆነ ከደረሰ በኋላ መንግሥት እያሳዬ ያለው ለዘብተኛ አቋም መታረም እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት በመስጂዶች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንደሚደርስ መረጃዎች እንደነበሩት በማንሳትም ቅድመ መከላከል አልሠራም በሚል ወቅሰዋል፡፡ ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላም በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው ተጠርጣሪዎች ቁጥር አነስተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት የተቃጠሉ ቤተ እምነቶችን እንዲሠራና የተዘረፉ ንብረቶችን እንዲመለሱ ማድረግ እንደለበትም ተናግረዋል፡፡
ችግሩ እንዲባባስም ሆነ የቤተ እምነቶች እንዲቃጠሉ የሚዲያ አካላት ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነም ነው ተወያዮቹ ያነሱት፡፡ የሚዲያ አውታሮች በተለይ በመስጂዶች ላይ ጥቃት ሲደርስ የሚሰጡት ሽፋን ሚዛናዊ እንዳልሆና መታረም እንደሚገባውም መክረዋል፡፡ መንግሥት የተቃጠሉ ቤተ እምነቶችን እንዲሠራና የተዘረፉ ንብረቶችን እንዲያስመልስም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ተመስገን አሰፋ
አዘጋጅ፡- ኃይሉ ማሞ
