
ባሕር ዳር: ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ ሀሳብ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሐ ግብር አካል የሆነው በአማራ ክልል በአንድ ጀምበር 260 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሐ ግብር እየተካሄደ ይገኛል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ.ር) መርሐ ግብሩን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በክልላችን የደን ሽፋን መራቆት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸው ከ54 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በአፈር መከላት ምክንያት ወደ አሲዳማነት መቀየሩን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ የደን ልማታችንን በማሳደግ የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ከፍተኛ የሆነ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሥራ ተከናውኗል ያሉ ሲሆን በተሰሩ ሥራዎችም ከ6 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ከ700 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ መተከላቸውን እና ከ80 በመቶ በላይ መፅደቅ መቻላቸውን ተናግረዋል።
በተከታታይ በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች የክልሉን የደን ሽፋን መጠን ከነበረበት 14 በመቶ ወደ 16 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉንም ጨምረው ተናግረዋል። የአፈር መከላትን ወደ 22 በመቶ መቀነስ መቻሉንም ገልጸዋል።
በዘንድሮው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ1 ነጥብ 7 በላይ ችግኞች መፈላታቸውን የገለጹት ቢሮ ኃላፊው ከነዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን እና በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ሰኔ 10/2015 ዓ.ም በክልል ደረጃ የዓመቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በይፋ ተከፍቶ በሁሉም አካባቢዎች ተግባሩ እየተከናወነ እንደሚገኝ በመግለጽ የዚሁ አካል የሆነው እና ሁለተኛው ምዕራፍ በአንድ ጀምበር 260 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የማስጀመሪያ ፕሮግራሙ ዛሬ ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም በይፋ ተጀምሮ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ኅብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ ችግኞችን እየተከለ እና አሻራውን እያሳረፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ ሥራችንን ዕቅድ በማሳካት የራሳችንን ሪከርድ መያዝ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን እና ይሄን ለማሳካትም ከንጋት እስከ ምሽት ተከላዎች በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እየተከናዎኑ መሆናቸውን ገልጸዋል። ከ5 ሺህ 600 በላይ የተከላ እንቅስቃሴዎችን እየተከታተሉ መረጃ የሚይዙ ባለሞያዎች መሰማራታቸውን አንስተዋል።ዘገባው የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
            
		