
የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ታኅሣሥ 10 ቀን 2012ዓ.ም ምሽት በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ አስተዳደር በሃይማኖት ተቋማትና በግል ንብረት ላይ ደረሰውን የቃጠሎ ጥቃት በማውገዝ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።
የቦርዱ ሰብሳቢ መልአከ ሠላም ኤፍሬም ሙሉዓለም እንደገለጹት የሰው ልጅ ከፈጣሪው ከተሰጠውን ሃይማኖታዊ ግብረ ገብነት በመውጣት በራሱ ሊደረግ የማይፈልገውን ነገር በሌሎች ላይ ማድረግ ተቀባይነት የለውም።
‹‹ቤተ እምነት ሰዎች ችግራቸውንና ደስታቸውን ለፈጣሪያቸው የሚነግሩበት፣ ትምህርት የሚያገኙበት፣ ፍቅር እና ሠላም የሚሰበክበት፣ ሕሙማን የሚፈወሱበት እና የተለያዩ የአምልኮ ሥርዓቶች የሚከወኑበት ነው›› ያሉት መልአከ ሠላም ኤፍሬም እነዚህን ተቋማት በእሳት ማቃጠል በምድራዊ እና ሠማያዊ መንግሥት እንደሚያስጠይቅም አስገንዝበዋል።
መልአከ ሠላም ኤፍሬም ሙሉዓለም እንደገለጹት የሁሉቱ የእምነት ተከታዮች ቤተ እምነቶቻቸውን ሲሠሩም ሆነ ሲያስመርቁ በጋራ፣ አብረው የሚበሉ እና የሚጠጡ ሕዝቦች እንጂ ለዘረፋና ለንብረት ውድመት የሚዳረሱ አይደሉም።
መንግሥትም ችግር ከመፈጠሩ በፊት ቀድሞ እንዲከላከልና ድሮጊቱ ከተፈጸመም በኋላ ፈጥኖ ለሕግ የማቅረብ ግዴታውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
‹‹ወጣቱም ከስሜት ወጥቶ አካባቢውን መጠበቅ እና ችግር ፈጣሪዎችን መምከር ይገባል›› ብለዋል መልአከ ሠላም ኤፍሬም። ንብረታቸው የወደመባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎን ንብረታቸውን በመተካት የድሮ ፍቅር እና አብሮነትን ማጠናከር እንደሚገባም የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው ሰብሳቢ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
