የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በቡሬ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች ችግኞችን እየተከሉ ነው።

14

ባሕር ዳር: ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “ነገን ዛሬ እንተከል” በሚል መሪ መልዕክት በአንድ ጀምበር የችግን ተከላ መርሐ ግብር በቡሬ ከተማ በግል ተቋማት፣ በመንግሥት ሠራተኛውና በመላ ማኀበረሰቡ 4 መቶ ሺህ የሚጠጋ ችግኝ ተተክሏል።

የፌቤላ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኀበር ሠራተኞችና መሪዎችም የከተማ አሥተዳደሩ ባዘጋጀላቸው ቦታና በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ችግኝ ተክለዋል።

የፌቤላ ኢንዱስትሪ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኀበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንየው ዋሴ ከ1ሺህ በላይ የፋብሪካው ሠራተኞች በችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ተሳትፈዋል ብለዋል። ሠራተኞቹም የዚህ ታሪክ አካል በመኾናቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል። የተከሏቸውንም ችግኞች ተንከባክበው ለማሳደግ ዝግጁ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

በዛሬው እለት እንደ ሀገር በተከናወነው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በከተማ አሥተዳደሩ 4 መቶ ሺህ የሚጠጋ ችግኝ መተከሉን የቡሬ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አበጀ ሙላት ተናግረዋል።

በቡሬ ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ እንደ ፌቤላ አይነት የፋብሪካ ተቋማት በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም ነው ምክትል ከንቲባው ያስታወቁት።

በዞኑ በዛሬው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር 30 ሚሊዮን የሚጠጋ ችግኝ እንደሚተከል የተናገሩት ደግሞ የምዕራብ ጎጃም ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኀላፊ ዘመኑ ታደለ ናቸው።

በምዕራብ ጎጃም ዞን በተያዘው የክረምት አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 206 ሚሊዮን የሚጠጋ የደንና ፍራፍሬ ችግኞች እንደሚተከሉ ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ዘጋቢ:-ዘመኑ ይርጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ማጽደቅና ለውጤት ማብቃት ይገባል” አምባሳደር ሐሰን አብዱልቃድር
Next articleየውጭ ሀገራት መገናኛ ብዙኃን በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል መርሐ-ግብርን ሽፋን ሰጥተው እየዘገቡ ይገኛሉ።