“የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ማጽደቅና ለውጤት ማብቃት ይገባል” አምባሳደር ሐሰን አብዱልቃድር

18

ባሕር ዳር: ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የተተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ ማጽደቅና ለምግብ ዋስትና ጠቀሜታ እንዲውሉ ማድረግ ከሁሉም ይጠበቃል ሲሉ አምባሳደር ሐሰን አብዱልቃድር አሳሰቡ።

የብልጽግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስተባባሪ አምባሳደር ሐሰን አብዱልቃድር የተመራ የፌደራል ቡድን በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ዙሪያ ወረዳ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራውን አኑረዋል።

በዚህ ወቅት አምባሳደሩ እንዳሉት ዛሬ በአንድ ጀምበር ለመትከል የታቀደው 500 ሚሊዮን ችግኝ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ርብርብ ሊያደርግ ይገባል።

ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን በአግባቡ ተንከባክቦ ማጽደቅና ለምግብ ዋስትና ጠቀሜታ ማዋል ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር መሆኑንም አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የተተከለው ችግኝ የደን ሽፋን ለማሳደግ፣ የአየር ንብረትን ለማስተካከልና የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ አይነተኛ ሚና መጫወቱንም አምባሳደር ሐሰን ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡ አንድነቱንና ሰላሙን ጠብቆ በልማቱ እያደረገ ያለው ተሳትፎ መልካም መሆኑን ጠቅሰው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የህብረተሰቡን አብሮነት የበለጠ ማጠናከሩንም አመልክተዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን በበኩላቸው በዞኑ ባለፉት አራት ዓመታት በተተከሉ ችግኞች የዞኑ የደን ሽፋን ከ9 በመቶ ወደ 13 በመቶ ከማደጉ ባለፈ አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን እንዲረጋገጥ እያገዘ ነው።

የተራቆቱ ተራራማ አካባቢዎች ማገገማቸውን ጠቁመው፣ በክረምት ወቅት እና ዛሬ በአንድ ጀምበር የሚተከሉ ችግኞች ውጤቱን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

በደሴ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደር አስናቀች ካሳው ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች ለአካባቢው ኅብረተሰብ ጥቅም መስጠት እንደጀመሩ ጠቁመው፣ በተለይ የእርሻ ማሳ በጎርፍ እንዳይሸረሸር በማድረግ የግብርና ምርታማነት መጨመሩን ገልጸዋል።

ተራሮችን በተፋሰስ በማልማት ለልጆቻችን የሥራ እድል ለመፍጠር የበኩላችንን እየተወጣን ነው” ያሉት አርሶ አደሯ፣ “የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር ችግኝ መትከልን ባህል አድርገን እንድንይዝ ዕድል ፈጥሯል” ብለዋል።

በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ላይ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና የመንግሥት ሠራተኞች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ19 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እየተከለ መኾኑን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ገለጸ።
Next articleየአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በቡሬ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች ችግኞችን እየተከሉ ነው።