
በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር 80 ሺህ በላይ ችግኞችን በመትከል ላይ መኾኑን የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር: ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር በዘንድሮው ክረምት 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት አድርጎ የችግኝ ተከላ እያካሄደ ነው የሚገኘው፡፡
ከተማ አሥተዳደሩ የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብርን ሳይጨምር እስካሁን ድረስ 750 ሺህ ችግኞች መትከሉን ገልጿል፡፡
በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ደግሞ 80 ሺህ ችግኞችን ለመትከል እቅድ ተይዞ 130 ሺህ ችግኞች መቅረባቸውን የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ ማርየ በለጠ (ዶ.ር) ገልጸዋል፡፡
ኀላፊው ለአሚኮ እንዳሉት ከተማ አሥተዳደሩ ባሉት የገጠር ቀበሌዎች 4 ተፋሰሶችን በመለየት ነው ችግኝ እየተከለ የሚገኘው፡፡
ከተከላ በፊት አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንና ከተከላ በኋላም ለኅብረተሰቡ በማስረከብ እንዲንከባከባቸው እንደሚደረግ ነው ያስገነዘቡት፡፡
ኅብረተሰቡ ከደን ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እንዲያገኝ ለማድረግ እንደሚሠራ የገለጹት ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ የደብረታቦር ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ታደለ እሸቴ ናቸው፡፡
በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ የከተማው ወጣቶች፣ የከተማው ዙሪያ ቀበሌ አርሶ አደሮችና በጎ ፈቃደኞች ተሳትፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
