“የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ግብን ለማሳካት ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል” የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አገኘሁ ተሻገር

68

ባሕር ዳር: ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በኢትዮጵያ እየተካሄደ በሚገኘው በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በደቡብ ክልል ሃድያ ዞን ተገኝተዋል። አቶ አገኘሁ እንዳሉት በሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት በተደረገው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ውጤታማ ሥራ ተሠርቷል። በተለይም ከሦስት ዓመታት በኋላ በዘመቻ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ሥራዎች በዓለም በተምሳሌታዊ ተግባር እየተፈጸመ ነው ብለዋል።

የዘንድሮው በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በመላው ኢትዮጵያ እየተከናወነ ነው ብለዋል። የሀገሪቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዛፍ ከመትከል የተሻገረ ዓላማን ያነገበ ነው ያሉት አፈጉባዔው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥም ታላሚ ተደርጎ እየተሠራ እንደኾነም ተናግረዋል።
በተለይም በዛሬው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በደቡብ ክልል በሀድያ ዞን እየተተከሉ ያሉ ችግኞች የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ ስለመኾናቸውም ነው ያስገነዘቡት።

በዞኑ ከፍተኛ የአቮካዶ ችግኝ ተከላ እየተካሄደ ነው ያሉት አቶ አገኘሁ የሀድያ ዞን በአቮካዶ ልማት ላይ ርብርብ ቢያደርግ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ይችላል ነው ያሉት። የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ከተረጅነት መውጣትና የሀገርን ክብር ማረጋገጥ ነው ብለዋል።

“የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ግብን ለማሳካት ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ይወጣ” ብለዋል አፈጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፡፡

ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ችግኞችን ከመትከል ባለፈ እንዲጸድቁ ጥበቃና እንክብካቤ ማድረግ ይገባል” የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ
Next article“አሁን የተገኘውን ሰላም በማጽናት የበለጠ የልማት ሥራ እንደሚሠራ አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።