
ገንዳ ውኃ: ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ሥነ ህይወታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ሀገር በቀል ችግኞችን በየዓመቱ በማፍላት እየተከለ ይገኛል። መምሪያው የ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት የአንድ ጀምበር አረንጓዴ አሻራ ልማት መርሐ ግብርን በመተማ ወረዳ ኮኪት ቀበሌ አስጀምሯል።
በዛሬው የአንድ ጀምበር አረንጓዴ አሻራ ልማት መርሐ ግብር በዞኑ በሚገኙ አራት ወረዳዎች እና በሦሥት ከተማ አሥተዳደሮች የችግኝ ተከላ ተግባር መከናወኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ አቶ ጤናው ለምለሙ ተናግረዋል።
እንደ ምክትል መምሪያ ኀላፊው ገለጻ የሚተከሉት ችግኞች የአካባቢውን ሥነ ምህዳር ከማስጠበቅና ምርታማነትን ከመጨመር ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ናቸው። ከእነዚህ ውስጥም እንደ አካሻ ሴኔጋል፣ ሽመል፣ ማንጎና ሚም ተጠቃሽ ናቸው። .
ችግኞችን ከማፍላትና የተከላ ቦታዎችን በጅፒኤስ ከመከለል በተጨማሪ የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ ጥበቃ እየተደረገላቸው መኾኑንም ተናግረዋል። ምዕራብ ጎንደር ዞን ከ6 መቶ 24 ሺህ በላይ የሚኾነው መሬት በደን የተሸፈነ ሲኾን አረንጓዴ መቀነት እየተባለ የሚጠሩት የአልጣሽና የጎደቤ ብሔራዊ ፓርክ እንዲሁም የማኀበረ ሥላሴ አንድነት ገዳም ጥብቅ ደን ሰፊውን ቦታ እንደሚይዙ ምክትል መምሪያ ኃላፊው ጠቁመዋል።
ዞኑ በየዓመቱ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ምህዳራዊ ፋይዳ ያላቸው ችግኞችን ከመትከል ባሻገር እነዚህን የተከለሉ ነባር የደን ቦታዎችን ከሰው ሰራሽ አደጋዎች መጠበቅና መንከባከብ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መኾኑንም አቶ ጤናው ተናግረዋል።
በመተማ ወረዳ የኮኪት ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት አቶ ኢብራሒም አካሉ እና አቶ ባዬ አደም በባለፈው ዓመት ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ጸድቀው አገልግሎት እንዲሰጡ እና ጉዳት እንዳይደርስባቸው በመጠበቅ እና በመንከባከብ ኀላፊነታቸውን መወጣታቸውን ተናግረዋል። በአካባቢያቸው የሚገኙ ጥብቅ ደኖች አደጋ እንዳይደርስባቸውም ክትትልና ቁጥጥር እያደረጉ መኾኑን ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት፡፡
በዛሬው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አሻራቸውን ማሳረፋቸውን ገልጸው ችግኞቹ በዘላቂነት ጸድቀው ጥቅም ላይ እንዲውሉ የበኩላቸውን ኀላፊነት እንደሚወጡ ነው የተናገሩት። በተከላ መርሐ ግብሩም የዞኑ የሥራ ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎችና የበጎ ፈቃድ ወጣቶች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ደሴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
