
ባሕር ዳር: ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የመከላከያ ሠራዊት አባላት በባሕር ዳር መኮድ ተገኝተው አሻራቸውን አስቀምጠዋል።
በስፍራው ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሰሜን ምዕራብ እዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ ሠራዊቱ ሀገር ከመጠበቅ ባሻገር የአየር ንብረት ለውጥን በመጠበቅ ሂደት የራሱን አሻራ እያኖረ ነው ብለዋል።
ሠራዊቱ በአንድ በኩል ድንበር ይጠብቃል በሌላ በኩል የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚደረገው ሂደት የራሱን ኀላፊነት እየተወጣ እንደኾነም ገልጸዋል።
በአንድ ጀንበር ግማሽ ሚሊዮን ችግኝ በሚተከልበት ታሪካዊ ቀን አሻራችንን እናስቀምጣለን ቀጣይነቱንም እናረጋግጣለን ነው ያሉት።
ሠራዊቱ ችግኝን ከመትከል ባሻገር መንከባከብ እና ለወደፊቱ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ማስረከብ ይጠበቅበታል፣ ይህንንም ግዳጅ በአግባቡ እየተወጣ ነው ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ለግጭት መንስኤ እየኾነ ነው ያሉት ሌተናል ጀነራሉ ኢትዮጵያ ይህን ችግር ለመቅረፍ ቀድመው ከተሠለፉት ሀገራት አንዷ መኾኗን አስረድተዋል።
ሌተናል ጀነራሉ የተሻለ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲመጣ ለማድረግ ሀገር በቀል ችግኞችን እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ችግኞች መተከላቸውንም አንስተዋል።
ለትውልድ አረንጓዴ ሸማ የለበሰች ኢትዮጵያን ለማስተላለፍ ኀላነታቸውን እየተወጡ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል።
የሰሜን ምዕራብ ዕዝ በጀት እና ፕሮግራም ኀላፊ ኮሎኔል ምህረት ሽፈራው ሠራዊቱ እንደሀገር የወረደውን ጥሪ ተከትሎ ዳግም ግዳጁን እየተወጣ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
ሠራዊቱ የተሠጠውን ግዳጅ እየተወጣ ነው የሚሉት ኮሎኔሉ ሠራዊቱ በልማቱ ላይ እየተሳተፈ ነው ብለዋል።
እያንዳንዱ እዝ የሚያለማው ቦታ እና ችግኝ ተሰጥቶታል በዚህ መሠረት ተከላው እየተካሄደ ነው፤ እንክብካቤውም ይቀጥላል ነው ያሉት።
ምክትል መቶ አለቃ ዙሪያሽ አለበል በበኩላቸው ለቀኑ ልዩ ስሜት አለኝ፤ ሠራዊቱ ካሁን በፊት ሀገር በመጠበቅ እየተወጣ ያለውን ኀላፊነቱን በልማቱ ላይም ለመድገም አሻራውን እያሳረፈ እና ድሉን እየደገመው ነው ብለዋል።
“የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ለውጤት እናበቃለን፤ ከእኛ አልፈው ለትውልድ የሚተላለፉ ለማድረግ እንክብካቤያችንን እንቀጥላለን ሲሉም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
