
ባሕር ዳር ከነማ በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረበትን ክፍተት በሁለተኛው አጋማሽ ማረሙ ውጤት እንዳስገኘው አሰልጣኙ ተናገሩ፡፡
በ4ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ ባሕርዳ ር ከነማ ድሬድዋ ከተማን 4ለ1 አሸንፏል፡፡
ለባሕር ዳር ከነማ ፍፁም ዓለሙና ማማዱ ሲድቤ ሁለት ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል፡፡
ለድሬድዋ ከነማ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረዉ ደግሞ ሪችሞንድ ኦዶንጎ ነው፡፡
ከባሕር ዳር ከነማ ሁለት ተጫዋቾችና ከድሬድዋ በኩል አንድ ተጫዋች ባልተገባ አጨዋወት ምክንያት የቢጫ ካርድ ሰለባ ሆነዋል፡፡
የባሕር ዳር ከነማ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ‹‹በሜዳችን ሁለተኛውን ጨዋታ በአሸናፊነት ተወጥተናል፣ የ90 ደቂቃ ጨዋታችንም ሁለት መልክ ነበረው›› ብለዋል፡፡
‹‹በመጀመሪያዎቹ 45 ደቂቃ ካጠቃን በኋላ ኳስ መልሰን ለማግኘት የነበረን የጨዋታ ፍጥነት ደካማ ነበር፤ በሁለተኛው 45 ደቂቃ ግን ጥሩ ተንቀሳቅሰናል፤ በውጤቱም ደስተኞች ነን›› ብለዋል፡፡
ከሜዳ ዉጭ ያላቸውን ደካማ የጨዋታ እንቅስቃሴና የተጫዋቾቻውን የሥነ ልቦና ለማሻሻል በሚቀጥሉት ጊዚያት ጠንክረዉ እንደሚሠሩም አሰልጣኙ ተናግረዋል፡፡
የድሬድዋ ከነማው አስልጣኝ ስምኦን ዓባይ በበኩላቸዉ ‹‹የዛሬው ጨዋታ ለእኛ ጥሩ አልነበረም፣ ጨዋታዉን ተበልጠን ነው ያጠናቀቅነው፣ ድሉም ይገባቸዋል›› ብለዋል፡፡
‹‹ካለፉት ሁለት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር የዘንድሮዉ ቡድን ያለዉ እንቅስቃሴ ደካማ ነው›› ያሉት አሰልጣኝ ስምኦን ቢሆንም ያሉትን ልጆች ተጠቅመው በቀጣይ ዉጤታቸውን ለማስተካከል ጥረት እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡
የጣናዉ ሞገድ ማሸነፉን ተከትሎ በ7 ነጥብና በ3 የግብ ልዩነት ደረጃዉን ወደ 3ኛ ከፍ አድርጓል፡፡
ትናንት የ4ኛ ሳምንት ጨዋታውን በሜዳው አድርጎ 3ለ0 ሀድያ ሆሳዕናን ያሸነፈው ፋሲል ከነማም ወደ 2ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል፡፡ ፋሲል ከነማ ከባሕር ዳር ከነማ እኩል 7 ነጥቦችን ሰብስቦ 7 የግብ ክፍያ በመያዝ ነው 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው፡፡ ሊጉን ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ 3 ጨዋታ አሸንፎና በ4ኛ ሳምንት ጨዋታው ትናንት አቻ ተለያይቶ በ10 ነጥብ እየመራ ነው፡፡
ዛሬ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የ4ኛ ሳምንት ጨዋታውን የሚያደርገው ሐዋሳ ከተማ በ7 ነጥብና 2 የግብ ከፍያ 4ኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ ሐዋሳ ከተማ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ነጥቡን 10 በማድረስ ከመሪው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ይስተካከላል፤ አቻም ከወጣ ባሕር ዳርና ፋሲል ከነማን በአንድ ነጥብ በመብለጥ ወደ 2ኛ ደረጃ ያድጋል፤ ከተሸነፈ ደግሞ በግብ ክፍያ በመቀሌ 70 እንደርታ ከተበለጠ ካለበትም ደረጃ ሊንሸራተት ይችላል፡፡
ዘጋቢ፡- ቻይና አየልኝ
