
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሕዋ ሳይንስ እና የሕዋ ቴክኖሎጂን ለማኅበራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት፣ ለአካባቢ ሀብት ጥበቃ እና አስተዳደር፣ ለአደጋ መከላከል ሥርዓት፣ ለሠላም እና ደኅንነት መከበር፣ ለሕዋ ምርምር፣ በሕዋ ዘርፍ ከሚሠሩ ሀገራት ጋር ዓለም አቀፍ ትብብር ለማጎልበት በእጅጉ ይጠቅማል፡፡
በኢትዮጵያ በሕዋ ሳይንስ ዘርፍ እንቅስቃሴ ማድረግ የተጀመረው በ1950 (እ.ኤ.አ) መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ የሥነ ፈለክ ቅኝት፣ ሳተላይት መከታተል እና ፎቶ ግራፍ ማንሳት እንዲሁም የሕዋ መረጃ ልውውጥ ተግባራት ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር ቀደም ባሉት ጊዚያት በጅምር ደረጃ ይከናወኑ እንደነበር ከስፔስ ፖሊሲ መጽሔት ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ ዘርፉ በ1960ዎቹ እና 1970ዎች (እ.ኤ.አ) ካሳየው መሻሻል አንፃር ሲታይ ደግሞ እስከ 2004 (እ.ኤ.አ) የጎላ እድገት ሳያሳይ ቆይቷል፡፡
በ2004 (እ.ኤ.አ) ‹የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ› መቋቋሙ ደግሞ በሀገሪቱ የሕዋ ሳይንስ ቴክኖሎጂ እንዲነቃቃ አድርጎታል፡፡ ጅምር እንቅስቃሴውን ወደ ተሻለ ሥራ ለማሸጋገርም በ2013 (እ.ኤ.አ) 32 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችን አንድ የግል ዩኒቨርሲቲንና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ቦርድን ባካተተ ሰብስበ የሚተዳደር የመጀመሪያው የምርምር ተቋም፤ እንጦጦ አብዘርባቶሪና ምርም ማዕከል ተቋቁሟል፡፡ ይህ ተቋም የሕዋ ፕሮግራም በመንደፍ ከሕዋ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ አተገባበር ጋር በተያየዘ ዕውቀት፣ ሙያዊ ክህሎት እና አቅም በመገንባት ለሕዋ ሳይንስ ቴክኖሎጂ እድገት የራሱን አስተዋፅዖ አብርክቷል፡፡፡ በተለይም አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ከዘርፉ ጋር ተያያዥነት ያለቸውን የትምህርት ፕሮግራሞች፣ ምርምር እና ሳይንሳዊ ጥናቶች የሚካሄዱባቸውን የግንባታ ፕሮጀክቶች በመንደፍ እንቅስቃሴዎች ሲያደርግ ቆይተዋል፡፡
የኢትዮጰያ መንግሥት ውጤታማ የሆነውን የስፔስ ፕሮግራም እንዲተገበር ኅዳር 2016 (እ.ኤ.አ) በሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንምብ ቁጥር 393/2016 የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ምክር ቤት እንዲሁም የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት የስፔስ ፖሊሲ ለማዘጋጅት ሀገር አቀፍ ጥናቶችን እንዳካሄዱ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
በዳሰሳ ጥናቱ መሠረትም ዝቅተኛ የሳይንሰ መሠረት፣ የተማረ የሰው ኃይል እጥረት፣ ደካማ የሕዋ ቴክኖሎጂ አቅም መኖር፣ እጅግ አነስተኛ የሕዋ መሠረተ ልማት፣ የሕዋ ጉዳዮች ቁጥጥር አለመኖር፣ ከሀገራዊ የልማት ፕሮግራሞች ጋር አለመናበብ፣ ዘርፉ የሥራ ዕድል ላያ አለመዋል፣ ግንዛቤ እጥረት እና የመሳሰሉት ጉዳዮች መኖራቸውም በጥናቶቹ ታይተዋል፡፡ ችግሮች ሙሉ በሙሉ ባይቀረፉም ኢትዮጵያ እነዚህን ችግሮች በማለፍ ታኅሣሥ 10 ቀን 2012 ዓ.ም የመጀመሪያዋን ሳታላይት አምጥቃለች፡፡
ሳታላይቷ ልዩ ልዩ ማኅበራዊ ምጣኔ ሀብት ችግሮች ላሉባት ሀገር በተለይም የምግብ ዋስትና እጥረትን፣ የማዕድን ሀብትን በበቂ ሁኔታ ለመጠቀም፣ የመሬት መረጃ ሥርዓት በማዘመን፣ የምድርን፣ የሕዋንና በራሪ አካላትን መሠረት አደረጎ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ያስችላል፡፡
በተለይም ከዘመናዊ የግብርና ሥራዎች ጋር በተያያዘ ምርታማነትን ለመተነበይና ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳዮችን ለመፈተሸ፣ የሥነ ምድር ጥናቶችን ለማካሄድ የጎላ አስተዋፆ እንዳለውም ይነገራል፡፡
ምንጭ፡- የኢፌዴሪ የስፔስ ሳይንስ ፖሊሲ (ታኅሳስ 2011ዓ.ም)
በአዳሙ ሺባባው
