“ችግራችን ለመፍታት አንድ እንሁን” ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

41

ባሕር ዳር: ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሐ ግብር በአማራ ክልል እየተካሄደ ነው፡፡

በመርሐ ግብሩ መልእክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) የአረንጓዴ አሻራን ግብ ለማሳካት በአለፉት አራት ዓመታት በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት፡፡ የተተከሉት ችግኞች አብዛኛዎቹ ጸድቀዋል፣ በመጽደቃቸውም በሥነ ምሕዳር ላይ ለውጥ አምጠተዋል ብለዋል፡፡

በክልሉ ደረጃ 260 ሚሊዮን ችግኞች በአንድ ጀምበር እንደሚተከሉም ገልጸዋል፡፡

“ነገን ዛሬ እንትከል” ለአማራ ክልል ዘርፈ ብዙ መልእክት አለው ያሉት ርእሰ መስተዳደሩ የመጀመሪያው ማጠንጠኛ የነገ ፍላጎታችን መሠረት የሚጣለው ዛሬ ነው፣ የነገ ሰላማችን፣ ልማታችን የሚመሠረተው ዛሬ በምንሰራው ነው ብለዋል፡፡

ልማታችን ለማፋጠን ሰላማችንን ማስከበር ይገባናል፣ የነገው ተስፋችን እንዲለምልም ሰላምን ለማስከበር ሁሉም ባለቤት ሆኖ የራሱን ጥረትና ርብርብ ማድረግ ይጠይቃልም ብለዋል፡፡

ሰላም ከደፈረሰ በኋላ መልሶ ለማረጋገጥ ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ ያነሱት ዶክተር ይልቃል የሰላም እጦት የሚያመጣው ቀውስ የሚታወቀው ሰላም የታጣ ጊዜ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ሰላምን የምናስከብረው በመተባበር እና በአንድነት ነውም ብለዋል፡፡ ልዩነቶችን ወደ ግጭት ሳይሆን ወደ ውይይት እና ወደ ድርድር ማምጣት እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

ዛሬ ላይ ያሉ ልዩነቶችን በውይይት እና በድርድር መፍታት የነገ ተስፋን የለመለመ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል፡፡

ለነገው ዛሬ መትከል አለብን ሲባል ለችግኝ ብቻ ሳይሆን ለሰላምም ነው ብለዋል፡፡

የነገ ልማታችን እና ፍላጎታችን ቀጣይነት እንዲኖረው፣ የተሟላ እንዲሆን ሰላማችን ለማስከበር ርብርብ ማድረግ ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡

ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች በተለመደው የባሕል አሠራር መሠረት ችግሮችን በራሳችን ለመፍታት ተዘጋጅተን መረባረብ ይኖርብናል፤ ይሄን እንድታደርጉ ጥሪየን አስተላልፋለሁ ብለዋል ርእሰ መስተዳድሩ፡፡

ዛሬ ሳንተክል ነገ ፍሬ መጠበቅ አንችልም፣ ዛሬ መሥራት ዛሬ መትከል አለብን ብለዋል፡፡ የነገውን ወጣት ዛሬ ላይ ኮትኩተን ማሳደግ አለብን፣ ያለበለዚያ የበቃና ሀገርን የሚረከብ ትውልድ መፍጠር አይቻልም ነው ያሉት፡፡ ለነገው ትውልድ ዛሬ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ችግኝ እየተከሉ ያሉት በጣና ዳርቻ መሆኑን ያወሱት ርእሰ መስተዳድሩ ችግኝን መትከል ዓባይን እና ጣናን ለመጠበቅ ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ነው የገለጹት፡፡
ሁሉም በባለቤትነት እና በኃላፊነት መትከል እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡

በአንድ ጀምበር ብቻ ተክሎ መተው ሳይሆን ቀጣይነት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው ያስገነዘቡት፡፡

በአማራ ክልል በተያዘው ክረምት 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉ ነው ያመላከቱት፡፡

አንድነት ኃይል ነው፣ መሰባሰብ መተባበር ችግርን ይፈታልም ብለዋል፡፡

ችግኝ መትከል እና የግብርና ሥራው የማይነጣጠል መሆኑንም አንስተዋል፡፡ ችግኞችን ለአካባቢው ጥቅምና አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ዋና ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በመተባበር እና በአንድነት ከሠራን የማንፈታው ችግር የለምም ብለዋል፡፡ ችግራችን ለመፍታት አንድ እንሁን ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በአንድ ጀምበር 24 ሚሊዮን ችግኞች ይተከላሉ ” የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ
Next articleበኦሮሚያ ክልል በጅማ ከተማ እና ማና ወረዳ የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው፡፡