“የአረንጓዴ አሻራ አብሮነትን እና አንድነትን የሚያጠናከር ነው” ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ

34

ባሕር ዳር: ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እየተካሄደ ነው፡፡ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርእሰ መሥተዳደር ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ወጌሾ የአረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡

ርእሰ መሥተዳድሩ ባስተላለፉት መልእክት በመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ አሻራ ከ650 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን አስታውቀዋል፡፡

ዘንደሮ በክልሉ ቀደም ብሎ ዝናብ በመጣሉ ከሚያዝያ ወር አጋማሽ ጀምሮ ችግኞ እየተተከሉ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

እስካሁንም ከ87 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በክልሉ መተከላቸውን ነው የገለጹት፡፡

በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ተከላውን እያከናወኑ መኾናቸውን ነው የገለጹት፡፡

በአንድ ጀንበር 20 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል እቅድ መያዙን አስታውቀዋል፡፡ እንደ ክልል በዓመቱ 300 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል እቅድ መያዙንም ተናግረዋል፡፡

ችግኝ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ትልቅ ትርጉም እንዳለው ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ ከአሁን ቀደም በተተከለው ችግኝ እና ባለው ደን ምክንያት ከቆላማ አካባቢዎች ውጭ ለዘጠኝ ወራት ዝናብ መኖሩንም አንስተዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ከደን በርካታ ጥቅሞችን እያገኘ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም የቡና፣ የማርና ሌሎች ምርቶችን ከደን እንደሚያገኙም ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ሕዝብ የደንን ጥቅም ከጥንት ጀምሮ ጠንቅቆ የሚያውቅና አሁንም በትኩረት የሚሠራ መኾኑን ነው ያነሱት፡፡ ችግኝ ተከላ በቀጥታ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመኾኑ ሕዝቡ የራሴ ብሎ እየሠራ ነውም ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ለሶማሊያ ክልል ከ219 ሺህ በላይ ችግኞችን ማበርከቱንም ገልጸዋል፡፡ ይህም አብሮነትን እና አንድነትን የሚያጠናከር መኾኑን ነው ያነሱት፡፡ የአረንጓዴ ልማት ሥራ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ነው፣ ወደ ፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የተሻለ የአየር ንብረት ለጤና ዋነኛ መሰረት በመኾኑ የዛሬዉን የችግኝ ተከላ በተገቢዉ መንገድ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል” የጤና መኒኒስቴር ዴኤታ አየለ ተሾመ (ዶ.ር)
Next article“እስከ ረፋዱ 3 ሰዓት ባለው የተከላ መርሐ ግብር 147 ሚሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ