
ባሕር ዳር:ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በችግኝ ተከላው የአማራ ክልል ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ባለሥልጣን አቶ ዘውዱ ማለደን ጨምሮ ፣የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ አቶ ጌታቸው አዳነ በዞኑ ለአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ ከ 332 ሺህ በላይ ችግኞች እንደሚተከሉ ተናግረዋል። ከ 370 ሺህ ሄክታር በላይ የተራቆቱ አካባቢዎች በችግኝ ይሸፈናሉም ብለዋል።
ችግኞች የሚተከሉበት ከ 30 በላይ ቀበሌዎች፣ ተፋሰሶችና የሚተክል ማኅበረሰብ ተዘጋጅቶ ካደረ በኋላ ዛሬ በኹሉም ወረዳዎችና ከተማ አሥተዳደሮች እየተተከለ መኾኑን ገልጸዋል።
የምዕራብ ጠለምት ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ስለሽ በርሄ እንደገለጹት በወረዳው ለአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 47 ሽህ ችግኝ ለማዘጋጀት ታቅዶ 90 ሺህ የሚኾኑ የደንና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተዘጋጅተው በወረዳው ኹሉም ቀበሌዎች ተከላው እየተከናወነ ይገኛል።
በተከላው ከ 6 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ መኾናቸውም ተገልጿል።
በዞኑ ለአንድ ቀን ጀንበር ተከላ የተዘጋጁ ኹሉም ችግኞች እስከ ቀኑ 12:00 ተተክለው ይጠናቀቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።
ዘጋቢ:- አድኖ ማርቆስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
