“በችግኝ ተከላ አሻራችንን በማሳረፍ የአካባቢያችንን ገፅታ እንቀይራለን” የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች

58

ባሕር ዳር: ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ነገን ዛሬ እንትከል በሚል መሪ መልዕክት የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።

ልጃቸውን አዝለው ችግኝ ሲተክሉ ያገኘናቸው ወይዘሮ እቴኑ ንጉሴ የተራቆተውን አካባቢ አረንጓዴ ለማልበስ ችግኝ መትከል ለነገ የማይባል ተግባር መኾኑን ተናግረዋል።

ለልጆቻችን ምቹ ከባቢ ለማስረከብ ችግኝ መትከልና በመንከባከብ የዜግነት ግዴታ ነው ያሉት ወይዘሮ እቴኑ ወጣቶችም የዚህ ተሳታፊ መኾን ይገባቸዋል ነው ያሉት።

ወይዘሮ ፋንታነሽ መንግሥቱም የአካባቢያችንን ገጽታ ከመመለስ ባለፈ ለከተማ ውበት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አሻራ የሚጥል ነው ብለዋል።

እኔ ዛሬ የተከልኩትን ችግኝ እንከባከባለሁ፤ ለልጅ ልጆቼም ምቹ ከባቢ ለማስረከብም እተጋለሁ ብለዋል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በ6 ወረዳዎች በ36 የተከላ ቦታዎች ላይ 398 ሺህ ችግኝ የመትከል ሥራ እየተካሄደ መኾኑን ነው የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የግብርና መምሪያ ኀላፊ አዲስ ወልዴ የተናገሩት።

የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ዝናብ አጠር በኾኑ አካባቢዎች አይነተኛ አማራጭ ነው ያሉት አቶ አዲስ በባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች ተስፋ ሰጭ የፅድቀት መጠን ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መላሽ ወርቃለም እንዳሉት ኢትዮጵያን ወደ ቀደመ ልምላሜዋ ለመመለስና በረሃማነትን ለመከላከል አረንጓዴ አሻራ ጉልህ ሚና መኖሩን ገልጸዋል፡፡ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በከተማ አሥተዳደሩ የተተከሉ ችግኞች አብዛኛዎቹ ፀድቀዋል ብለዋል።
ይህም የከተማውን ገፅታ ከመመለስ ባለፈ ለገቢ ማስገኛነት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ትልቅ ተስፋ እንደተጣለባቸው አቶ መላሽ ተናግረዋል።

አካባቢው ዝናብ አጠር በመኾኑ የተፈጥሮ ሃብት መመናመን ችግርን ለመከላከል የአረንጓዴ አሻራ የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ፡- ሰሎሞን ደሴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሚያምርብን ስናብር ነው፤ አብሮ ታሪክ መሥራት ከሁሉም በላይ ትልቁ ድል ነው ” አቶ ደመቀ መኮንን
Next articleበአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በምዕራብ ጠለምት ወረዳ ዞናዊ የአንድ ጀምበር አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ እየተካሄደ ነው።