
ባሕር ዳር: ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአዲስ አበባ የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ባስተላለፉት መልዕክት እንኳን ታሪክ ለመስራት አበቃን ብለዋል፤ እያንዳንዱ ቀን ለሀገር በልማትም፣ በጉድለትም ሊመሰል ይችላል፣ የዛሬው ቀን ትልቅ ታሪክ እየተሰራበት ያለ ቀን ነው ብለዋል፡፡
500 ሚሊዮን ችግኝ በአንድ ጀምበር ለመትከል በኢትዮጵያ ምድር በሁሉም ማዕዘናት ሁሉም እየዘመተ ታሪክ እየሠራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ሀገርን በማልበስ ለነገ ትውልድ ለማውረስ ትልቅ ቁም ነገር እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የይቻላል ውጤትን የምናሳይበት እለት ነውም ብለዋል፡፡
500 ሚሊዮን ችግኝ መትከል ቁጥር ብቻ አይደለም በጀርባው ብዙ ሚስጥሮች እና ቁም ነገሮች አሉት ነው ያሉት አቶ ደመቀ፡፡
የእኛን የራሳችን የመስራት አቅም የበለጠ ያነሳሳል፣ ለመጪው ዘመን ለተሻለ እንዘጋጅበታለን፣ ክብረ ወሰን እያሻሻልን፣ የዓለምን ክብረ ወሰን በከፍተኛ ደረጃ የምንመራበት ነውም ብለዋል፡፡ ዓለም እየተፈተነች ካሉበት አንዱ የአየር ንብረት መዛባት ነው ያሉት አቶ ደመቀ ሀገርን ቀድሞ ወደነበረችበት እና ወደ ተሻለ ለማምጣት ለዓለም ተምሳሌት ለመሆን ኢትዮጵያ ተሰልፋለች ብለዋል።
ይህ ትውልድ እድለኛ ነው፣ የራሱን ታሪክ ይሠራል፣ የተመቸች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ተዘጋጅቷል ነው ያሉት፡፡ በታሪክ ሰሪነታችን ልንኮራበት፣ ለላቀ ሥራ ልንሰማራበት የምንችልበት ነውም ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ በየመንደሯ ድግስ ላይ ትገኛለች ነው ያሉት አቶ ደመቀ፡፡ የአንድ ጀንበር ዘመቻ በራሱ አንድ ስኬት ነው ያሉት አቶ ደመቀ ቀጣይ ለሚኖረው ደግሞ መነሻ ነውም ብለዋል፡፡
መንግሥት ጥሪውን አቅርቦ ሲሰለፍ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን ለመስጠት ሲሰለፍና ሲተባበር ማየት የሚያኮራ መሆኑንም ገልጸዋል፤ ማበር ምን ያክል ያኮራል ያሉት አቶ ደመቀ የሚያምርብን ስናብር ነው፣ አብሮ ታሪክ መሥራት ከሁሉም በላይ ትልቁ ድል ነው ብለዋል፡፡
ችግኝ ስንተክል በአንድ ጊዜ ተክለን አንሰናበትም፣ እንደ ልጆቻችን እንከባከበዋለን፣ አሻራችንን መልሰን እናየዋለን እንጂ ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያ የያዘችውን ስኬት ይዛ ለመዝለቅ እየሠራች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
