
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩንኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ይርሰው በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
ትናንት ታኅሣሥ 10 ቀን 2012ዓ.ም በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ አስተዳደር በተነሳው አለመረጋጋት ጉዳይ መግለጫ የሰጡት አቶ ጌትነት ይርሳው ችግር ዒላማ ያደረገው የሃይማኖት ተቋማት ላይ እንደነበር አስታውቀዋል። “ድርጊቱ በፍቅርና በአንድነት አብረው የኖሩትን የሁለቱን ሃይማኖት ተከታዮች ለማጋጨት የተደረገ ነው “ብለውታል። “ኢትዮጵያ አንደነቷ የጠነከረ ታላቅ ሀገር እንዳትሆን የሚጥሩ ዋነኛ ጠላቶቿ ሁሉ ቀዳሚ ዒላማቸው የሃይማኖት ተቋማትና አማራ መሆኑ ታውቆ ያደረ ነው” ሲሉም ገልፀዋል።
“የአማራ ሕዝብ በልዩ ልዩ መልኩ ይፈተናል” ያሉት ዳይሬክተሩ በድንበር፣ በብሔር፣ በሃይማኖትና በማንነቱ እንደሚፈተን አመላክተዋል። “ነገር ግን ማንኛውም ፈተና የአማራን ሕዝብ ሊያንበረክከው አይችልም”ብለዋል። የአማራ ሕዝብ በአርቆ አሳቢነትና በአስታዋይነት ከፍ ያለ ልዕልና እንዳለው ያነሱት ዳይሬክተሩ ቸግሮችን እንደ አመጣጣቸው ተገቢና ሕጋዊ የሆነ መልስ ይሰጣቸዋልም ብለዋል።
ትናንት የተከሰተው የግጭቱ ዋነኛ ዒላማ የኦርቶዶክስ እና የእስልምና አማኞች መሆናቸውን ያስታወቁት አቶ ጌትነት “የግጭት እሳት በመለኮስ ወደሌሎችም አስፋፍቶ ለክልሉ ሕዝብ ተጨማሪ አጀንዳ መስጠትና አማራውን የማዳከም ስልት ነው” ብለዋል። በጊዮርጊስ ቤተ ክርስትያን የደረሰው የቃጠሎ ሙከራ ከከሸፈና የሃይማኖት አባቶች ሙከራውን ላከሸፈው ታዳሚ ምርቃት ሰጥተው ወደየቤቱ ከሸኙ በኋላ ጉዳዩን ሌላ መልክ በማስያዝ መጅዶች ላይ ጥቃት እንደተፈጸመም ነው የገለፁት። አጋጣሚውን በመጠቀምም ሱቆች ላይ ጉዳት በማድረስ ንብረት መወደሙንም ገልጸዋል።
“በሰው ላይም ቀላልና ከባድ ጉዳት አድርሰዋል” ነው ያሉት። መግለጫው እስከተሰጠበት ጊዜም የሰው ሕይወት አላለፈም ነው የተባለው። የክልሉ የፀጥታ ኃይል አካባቢውን ተቆጣጥሮት እንደሚገኝ የገለፁት አቶ ጌትነት ከጠዋት ጀምሮ ውይይት እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል። አምስት ድርጊቱን አቅደው መርተዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው መረጃ እየተጣራባቸው እንደሆነና ሌሎችንም ለመያዝ እየተሠራ እንደሆነም ነው የገለፁት።
“!የተፈጠረውን ድርጊት የክልሉ መንግሥት በፅኑ እንደሚያወግዘው የገለፁት አቶ ጌትነት “ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን በአጥፊዎች ላይ አስፈላጊ የሆነ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል” ነው ያሉት። የአማራ ክልል መንግስትም በደረሰው ችግር ማዘኑን ነው የገለፁት። ችግሩን ለመፍታትም የክልሉ መንግሥት ከማኅበረሰቡ ጎን እንደሚቆም ነው ያረጋገጡት። የአማራን ሕዝብ ከፍ ካለ የሥነ ልቦና ልዕልናው ለማውረድ የሚጥሩ ኃይሎችን እንደተለመደው በአንድነት በመቆም እኩይ ዓላማቸውን እንዲያከሽፍ በክልሉ መንግሥት ስም ጥሪ አቅርበዋል።
“የሞጣ ሕዝብ ለሌሎች አካባቢዎች አራዓያ መሆን የሚችል የሚያስቀና ሕዝብ ነው” ያሉት አቶ ጌትነት “በርካታ ፈተናዎች አሉብን፤ ነገር ግን የክልላችን የፀጥታ ኃይል እየተከታተለ እያከሸፈ ነው” ብለዋል። ሕዝቡም ለጥቃት እንዳይዳረግ ከፍተኛ የሆነ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል። የነበረው ችግር ወደከፋ ደራጃ እንዳይደርስ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሞጣ ሕዝብ ከፀጥታ አካለት ጋር በመሆን ችግሩን ማብረዱንም ገልጸዋል።
አጥፊዎቹን ለመለዬትም ጉዳዩ በሕግ አግባብ እንደሚታና አጥፊዎችንም በሕግ መሠረት ለመቅጣት የክልሉ መንግሥት እንደሚሠራ አቶ ጌትነት አስታውቀዋል። “አማራን አንገቱን አስደፍተው እነርሱ ቀና ለማለት የሚጥሩ አካት አሉ፤ ይህን ችግር ግን በጋራ እንደምንወጣው አንጠራጠርም” ብለዋል። ለዘመናት በአብሮንት የቆዩት የሁለቱ የሃይማኖቶች ተከታዮችም እኩይ ተግባር ባላቸው አካላት አብሮነታቸው እንደማይሸረሸር አመልክተዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
