በሀረሪ ክልል የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።

59

ሀረሪ: ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) 500 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀንበር የመትክል መርሐ ግብር በሀረሪ ክልል እየተከናወነ ነው፡፡

የሀረሪ ክልል ርእሰ መስተዳደር ኦድሪን በድሪ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ችግኝ ተክለዋል፡፡ ርእሰ መስተዳድሩ በክልሉ በአንድ ጀንበር 350 ሺህ ችግኞችን እንተክላን ብለዋል፡፡ 30 ሺህ ዜጎች ደግሞ በችግኝ ተከላው መርሃ ግብር ይታሰፉበታል ነው ያሉት፡፡

የክልሉ ሕዝብ ከማለዳ ጀምሮ የችግኝ ተከላውን እያከናወነ ነው ብለዋል። የችግኝ መርሃ ግብሩ እንደሚቀጥል የገለፁት ርእሰ መስተዳድሩ በክልሉ በአጠቃላይ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል እቅድ መያዙንም አንስተዋል፡፡

በአንድ ጀንበር ከሚተከሉት ችግኞች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ለምግብነት የሚያገለግሉ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ይህም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ለቀጣይ ትውልድ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡ ለመጪው ትውልድ የምግብ ዋስትናዋን ያረጋገጠች ሀገር መፍጠር አለብን ብለዋል፡፡ ኅብረተሰቡ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ እየተከታተለ እንዲጸድቁ ማድረግ ይገበዋልም ብለዋል፡፡

በሀረሪ እየተካሄደ ባለው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ላይ የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለምን ጨምሮ በርካታ የፌደራል የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብርን ባለሙያዎች በሁነት መከታተያ ክፍል እየተከታተሉ ይገኛሉ።
Next articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሃግብርን በአዲስ አበባ አስጀመሩ።