“ዛሬ ሁሉም ዜጋ የሀገሩን ፍቅር የሚያሳይበት ዕለት ነው” ሚኒስትር ዴዔታ ሠላማዊት ካሳ

53

ባሕር ዳር: ሐምሌ10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ሥራዋን በማለዳ ጀምራለች፡፡

በመላ ሀገሪቱ የተጀመረውን የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አስመልክተው ማብራሪያ የሰጡት የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ኢትዮጵያውያንን በመሉ አንድ የሚያደርጉን፣ በአንድ ዓላማ የሚያሰልፉን፣ አንዴ ተከስተው የሚጠፉ ሳይሆን ሁሌም ሕዝብን አንድ የሚያደርጉ፣ የሀገር ፍቅርን የሚያጠናክሩ ብዙ ክስተቶች አሉ ብለዋል፡፡

የሀገር ፍቅርን ከሚጨምሩ እና ሀገራዊ አንድነትን ከሚያመጡት መካከል የአረንጓዴ አሻራ አንደኛው ነውም ብለዋል፡፡

ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ችግኝ መትከያ ሥፍራዎች እየተመሙ መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡

አረንጓዴ አሻራ ባለፉት ዓመታት ሲተገበር እንደቆዬ ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ ብዙ ለውጦች ማምጣቱንም ተናግረዋል፡፡ በመጀመሪያው ምዕራፍ የሚታይ ለውጥ ያመጣ፣ እንደ ሀገር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሲሰራበት የቆየ መኾኑን አንስተዋል፡፡

አረንጓዴ አሻራ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ሳይቀር ሀገራዊ አንድነትን እና ሀገራዊ ጥንካሬያችንን ያሳየንበት ነበርም ብለዋል፡፡ አረንጓዴ አሻራ በዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት ውስጥ በጉልህ የሚጠቀስ ተግባር መኾኑን ገልጸዋል፡፡

አረንጓዴ አሻራ ከሀገራዊ ዋና ዋና ጉዳዮች ጋር አብሮ ሲሄድ የቆዬ፣ ሀገራዊ ድል የተመዘገበበት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የተገኘበት መኾኑንም አንስተዋል፡፡

ክረምት ሲመጣ የአረንጓዴ ባሕል እንዲሳል ያደረገ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ አረንጓዴ አሻራ ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ ሥራን መቀጠል እንደሚቻል የታየበት፣ በስኬት ብርታትን መሰነቅ የተቻለበት፣ ከፈተናዎች ትምህርት መውሰድ የተቻለበት፣ ሀገራዊ ትምህርት የተወሰደበት እና በአንድነት ያሰባሰበ ነውም ብለዋል፡፡

ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታትም ይተገበራል ተብሏል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት በትጋት የሚሰራበት መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ሥነ ሥርዓት ከማለዳው ጀምሮ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ሀገራዊ ጥሪውን ተቀብለው ሀገራዊ ዓላማውን በመያዝ እየተሳተፉ መኾኑም ተነስቷል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን በዓለም የያዝነውን ክብረ ወሰን ዛሬ የምናሻሽልበት ታላቅ ታሪካዊ እለት ነውም ብለዋል፡፡ በሀገራዊ ንቅናቄው ለትውልድ የሚጠቅም ሥራ የምንሰራበት፣ ለወደፊቱም ለሀገር የሚጠቅም ቁም ነገር መሥራታችንን በኩራት የምንመሰክርበትም ቀን ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ሁሉም ዜጋ ሀገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ሁሉም ዜጋ የሀገሩን ፍቅር የሚያሳይበት ዕለት ነው ብለዋል ሚኒስትር ዴዔታዋ፡፡

ከሶስት ሺህ በላይ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች መረጃዎችን እንደሚያደርሱም አንስተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሐምሌ 10 በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 10 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ዝግጅት አጠናቅቀናል” የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብርን እያካሄዱ ነው፡፡