
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 08/2012ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የክልሉን ሕገ መንግሥት መሠረት በማድረግ በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባሕሎች፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች እንዲጎለብቱ ለማሳደግ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ የራድዮ የአየር ሰዓት በመክፈት ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
አብመድ በከፈተው የአየር ሰዓት ስርጭት በክልሉ የሚገኙ የብሔረሰብ አስተዳደሮች ማለትም አዊ፣ ኦሮሞ እና ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ ተሞክሮዎች በሕዝብ ውስጥ እንዲንሸራሸር በማድረግ የጎላ ሚና ተጫውቷል፡፡ በወቅቱ የሬድዮ ጣቢያውን የሚያዳምጡ ሰዎች በብሔረሰብ ቋንቋ ስርጭት በመጀመሩ የተሰማቸውን ደስታ ሲገልጹ እንደነበር በወቅቱ የነበሩ ጋዜጠኞች ነግረውናል፡፡ በ1997 ዓ.ም የተጀመረው የብሔረሰብ ቋንቋዎች የመጀመሪያ ስርጭት የ15 ደቂቃ ሽፋን ነበረው፡፡
ድርጅቱ በየጊዜው የአድማጩን ፍላጎት የበለጠ ለማርካት በ2001 ዓ.ም ግንቦት ወር የ15 ደቂቃ የነበረውን የስርጭት ሰዓት ወደ አንድ ሰዓት ከፍ በማድረግ የብሔረሰቦች አስተዳድር ወቅታዊ መረጃ እና የመዝናኛ አገልግሎት እንዲያገኙ ጥረት አድርጓል፡፡ በዚህ ወቅት የሦስቱም ብሔረሰብ ቋንቋ የስርጭት መርሀ ግብሮች ጠዋት ከሦስት እስከ አራት ሰዓት ነበሩ፡፡ ነገር ግን ለብሔረሰብ ቋንቋዎች የተመደበው የአየር ሰዓት ለአብዛኛው ሕዝብ አመቺ አለመሆኑ በተከታታዮቹ በመገለጹ አብመድ የሕዝብ ጥያቄ መነሻ በማድረግ የአየር ሰዓት ለውጥም አድርጓል፡፡
‹‹ድርጅቱ የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የአየር ሰዓት ለውጥ በማድረጉም ምሽት እንዲሰራጭ በመወሰኑ በርካት አድማጮችን ማሳተፍ ችሏል›› ሲሉ በአብመድ የቋንቋዎች ዋና ዳይሬክተር ይፍቱሥራ ፋንታሁን አስረድተዋል፡፡
በቅርቡም የሕዝቡን የመረጃ ፍላጎት ለማርካት የአየር ሰዓት ለውጥ ብቻ ሳይሆን የአየር ሰዓት ማሻሻያም በማድረግ ለእያንዳንዳቸው የብሔረሰብ ቋንቋዎች በሳምንት የአራት ሰዓታት ስርጭት እንዲኖር ማሻሻያ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
የብሔረሰብ ቋንቋዎችን በሬድዮ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ሚድዬሞች ላይ ተሳትፎ እንዲኖራቸውም ተደርጓል፡፡ ጥቅምት 1/2003 ዓ.ም በብሔር አስተዳደሮቹ የተሰየመ ባለስምንት ገጽ ጋዜጦች ለሕትመት መብቃት ችሏለዋል፡፡ ጋዜጦቹ በወቅቱ እያንዳንዱ ብሔረሰብ ቋንቋ 1 ሺህ ቅጅ ያሉት ሲሆን የኅብረተሰቡ ጥያቄ እያደገ በመምጣቱ የእያንዳንዱ ብሔረሰብ ቋንቋ ጋዜጣ እስከ ስድስት ሺህ ከፍ ማለት ችሏል፡፡
በተጨማሪም በ2008 ሰኔ ወር የብሔረሰብ ቋንቋዎች በሳምንት የቴሌቪዥን የአየር ሰዓት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በሂደትም የአንድ ሰዓት ስርጭቱ ከስርጭት ማግስት በድጋሜ እንዲሰራጭ በመደረጉ ስርጭቱ ያመለጣቸው ደንበኞች በድጋሜ እንዲመለከቱ ዕድል ሰጥቷቸዋል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ ባለው የለውጥ ሂደት የብሔረሰብ ቋንቋዎች የራሳቸውን ድረገጽ በመክፈት ሕዝባቸውን በዲጂታል የመረጃ መረብ እንዲደርሱ ተደርጓል፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ ብሔረሰብ ቋንቋዎች የየራሳቸውን ገጽ በመክፈት ለደንበኞቻቸው ወቅታዊ መረጃዎችን እያደረሱ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ዘርፍ ውስጥ በጋዜጣ እና በቴሌቪዥን የታተሙት እና የተሰራጩ ዘገባዎች አንባቢው እና ተመልካቹ በቀላሉ እንዲያገኛቸው በማኅበራዊ ሚዲያ (ፌስቡክ እና ዩቲዩብ) እየተጫኑም ሌላ አማራጭ መዳረሻ ሆነዋል፡፡
የብሔረሰብ ቋንቋዎች የሰው ኃይልን በመጨመር ወቅቱ እና ጊዜው በሚዋጀው መሠረት እየተሻሻሉ በምምጣት ለሕዝቡ መረጃ በመስጠት፣ በማዝናናት እና በማስተማር እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ
