
አሶሳ: ሐምሌ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “ነገን ዛሬ እንትከል” የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቅቋል።
ክልሉ የሚታወቅበትን የቀርቀሃ እና ማንጎ ችግኞችን ጨምሮ ለታላቁ ህዳሴ የዓባይ ግድብ ፋይዳ ያለው ችግኝ ተከላ ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ የግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ በቀለ አንበሳ ገልጸዋል።
ሃምሌ 10 2015 ዓ.ም በመላው ኢትዮጵያ ነገን ዛሬ እንትከል በሚል መሪ ሃሳብ የራሳችንን ክብረ ወሰን ራሳችን እንድንሰብር ታስቧል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ይህንን ዕቅድ ለማሳካት ዝግጅት መጠናቀቁን አቶ በቀለ አንበሳው ለአሚኮ ተናግረዋል።
ቅድመ ዝግጅቱ የተጀመረው ዛሬ ሳይኾን ካላፈው ዓመት መስከረም ወር ጀምሮ የችግኝ ጣቢያ በማዘጋጀት፣ ዘር በመግዛት እና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችን በማዘጋጀት ነው ብለዋል።
እንደክልል በዚህ ዓመት በመደበኛና በአረንጓዴ አሻራ ቀን ለመትከል የተያዘው ዕቅድ 55 ሚሊዮን ችግኞች መኾኑን የጠቆሙት አቶ በቀለ ሀምሌ 10 በአንድ ጀምበር አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 10 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል መታቀዱን ተናግረዋል ።
ይህንን ለማድረግ አርሶ አደር፣ ባለሙያና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በቅንጅት ሲሠሩ ቆይተዋል ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የችግኝ ተከላው በይፋ የተጀመረው በክልሉ ፕሬዚዳንት አማካኝነት ሰኔ 24 መኾኑንም አስታውሰዋል።
የተደረገውን ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ ለአሚኮ ማብራሪያ የሰጡት አቶ በቀለ 519 ሺ ሄክታር መሬት መዘጋጀቱንና 85 ቦታዎች ለተከላው መለየታቸውን ገልጸዋል።
በነዚህም ቦታዎች 10 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸውን እና ፅድቀት አመቺ መኾናቸውን ማረጋገጥ በሚችልበት አኳዃን ተዘጋጅቷል ፣ ወደ አካባቢው ተጓጉዘዋል፤ ጉድጓዶችም ተቆፍረዋል ብለዋል።
ችግኞቹ ክልሉ የሚታወቅበትን 60 በመቶ የቀርቀሃ እና የማንጎ እና ቡና ዘሮች እንዲሁም 20 በመቶ ደግሞ ሌሎች የደን ችግኞች ይሆናሉም ተብሏል።
በተከላው የሃይማኖት አባቶች፣ የፌዴራል እና የክልሉ ከፍተኛ መሪዎችን ጨምሮ ከ500 ሺ በላይ ሕዝብ ይሳተፋል ነው ያሉት።
የፅድቀት መጠኑ የተሻለ እንዲሆን በየ3 ወሩ ኩትኳቶና ምንጣሮ የሚደረግ መኾኑን የገለጡት አቶ በቀለ ለህዳሴው ግድብ ቅርብ ከመሆኑ አንፃር ችግኝ ተከላው ፋይዳው ትልቅ ነው ይላሉ።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የግድቡ ውኃ የሚተኛበት ተብሎ የተመነጠረውን ደን ለማካካስም ከቦታው ከፍ ብሎ ለደለል እንዳይጋለጥ ችግኝ ተከላው ይከናወናል ተብሏል።
ክልሉ በቀርቀሃ ምርት የሀገሪቱን 62 በመቶ የሚሸፍን ሲሆን የክልሉ የደን ሽፋን 43 በመቶ መሆኑንና በዚህ ታሪካዊ መርሐ ግብር ይህንን ለማሻሻል ጥረት ይደረጋል ብለዋል አቶ በቀለ።
ዘጋቢ:- ድልነሳ መንግስቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
