
ባሕር ዳር: ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮች እና የሠራዊቱ አባላት በአንድ ቀን 500 ሚሊዮን ችግኞችን መትከልን ጨምሮ በክረምቱ በተያዘው ሀገሪቱን አረንጓዴ የማልበስ ዘመቻ በተሰማሩባቸው ቦታዎች ሁሉ አረንጓዴ አሻራቸውን እያኖሩ እንደሚገኝ ተገለጸ።
ሰራዊቱ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በማከናወን ኢትዮጵያን ወደ ቀደመ አረንጓዴነቷ የመመለስ ጥሪው ላይ በግንባር ቀደምትነት አሻራውን ለማኖር በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል ተብሏል።
ሰራዊቱ በተሰማራባቸው የሰላም ማስከበር ግዳጆች ውስጥ አህጉራዊና አለም አቀፋዊ የአረንጓዴ አሻራ የማኖር ተግባር ሲያከናውን የቆየ ሲሆን አሁንም በላቀ ሁኔታ ለመፈፀም መዘጋጀቱን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ሰራዊቱ በአረንጓዴ አሻራ ችግኞችን ሲተክል ችግር ፈጣሪዎችን በመንቀል ፤ የጀግኖችን ክቡር መስዋዕትነት በማስቀጠል ፤በደምና በመስዋዕትነት የተረከበውን አደራ እያስታወሰ በመሆኑ ትርጉሙም የጎላ መሆኑ ተጠቅሷል።
ሰራዊቱ ባስተላለፈው መረጃ ለልጆቻችን የምናወርሳት ሀገራችን በጀግኖች ልጆቿ ውድ መስዋዕትነት የተከበረች፤ ሁለንተናዊ ሉአላዊነቷ ፤ሰላሟ፤ ክብሯና ዕድገቷ የተጠበቀ፤ ከአየር ብክለት የፀዳች እና በአረንጓዴ የተሸፈነችና የበለፀገች እንደምትሆን አንጠራጠርም ብሏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
