
ደብረ ማርቆስ: ሐምሌ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ)መምሪያው የተጀመሩ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶችን በቀጣይ በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ እና የኅብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሥራ ግምገማ በደብረ ማርቆስ ከተማ አካሂዷል፡፡ በምሥራቅ ጎጃም ዞን የንጹህ መጠጥ ዉኃ ሽፋኑ ከ50 በመቶ በላይ ቢኾንም ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ለማድረግ 540 የንጹህ መጠጥ ዉኃ ተቋማትን በመገንባት በ2015 ዓም አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጓል፡፡ በ2015 በጀት ዓመት የዞኑን የንጹህ መጠጥ ዉኃ አቅርቦት እና ሽፋን በ3 ነጥብ 5 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉም ተገልጿል።
የዞኑ ዉኃ እና ኢነርጅ መምሪያ ኀላፊ ገደፋው ይርሳው እንደገለጹት በክልል፣ በሕዝብ ተሳትፎ እና በድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች በመታገዝ የኅብረተሰቡን የውሃ ፍላጎት እና ጥያቄ ለመመለስ እየተሠራ ነው፡፡ መምሪያው ኅብረተሰቡን የባዮ ጋዝ ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግም 930 የባዮጋዝ ተቋማትን መገንባት መቻሉን ኀላፊው ተናግረዋል፡፡
ወረዳዎች ባላቸው በጀት እና ኅብረተሰቡን በማስተባበር የውሃ ተቋማት እድሳት እና ግንባታዎችን በማጠናቀቅ የዜጎችን የውኃ ፍላጎት ጥያቄዎችን መቀነስ እንደቻሉ በግምገማ መድረኩ ተገለጿል፡፡ በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ዉኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ተስፋየ አባቡ በምሥራቅ ጎጃም እና ሌሎችም የክልሉ ዞኖች እና ወረዳ አሥተዳደሮች የመጠጥ ዉኃ አቅርቦትን ለማሳደግ የተጀመሩ የግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ክትትል እና ድጋፍ እየተደረገ መኾኑን አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ:- ግብረወርቅ ጌታቸው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
