“አምሳያ ለሌላት እናት፣ የተዋበውን ካባ አልብሷት”

61

ባሕር ዳር: ሐምሌ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የተዋበች ናት፣ የተዋበው ካባ ይገባታል፣ የተከበረች ናትና የክብር ጌጥም ይገባታል፣ ግርማና ሞገስ ለእርሷ ስጧት፣ ከጌጦች ሁሉ መርጣችሁ አስጊጧት፣ ከስጦታዎች ሁሉ የላቀውን እና የተወደደውን ሁሉ ስጧት፣ እርሷ ጠይቃችሁ አትከልክሏት፤ እርሷም ጠርታችሁ ዝም አትበሏት፣ ለምን ካሉ እርሷ እናት ናትና፣ እርሷ እትብት ናትና፣ እርሷ እርስት ናትና፣ እርሷ ውበት ናትና፣ እርሷ ማንነት ናትና፡፡

የትናንት ልጆቿ የጠየቀቻቸውን ሁሉ ሰጥተዋታል፣ ላብ በጠየቀች ጊዜ ላባቸውን፣ ደም በጠየቀች ጊዜ ደማቸውን፣ አጥንት በጠየቀች ጊዜ አጥንታቸውን፣ ሕይወት በጠየቀች ጊዜ ሕይወታቸውን ሰጥተዋታል፡፡ ሁሉን ጠየቋት፣ ሁሉን ሰጧት፡፡

የጠየቀቻቸውን ሁሉ ስለ ሰጧት በክብር አኖሯት፣ በታሪክ መዝገብ ላይ አደመቋት፣ በነጻነት ከፍ አደረጓት፣ በድል አድራጊነት አራመዷት፡፡ የእርሷ እውነተኛ ልጆች በጠራቻቸው ጊዜ በፍጥነት ይነሳሉ፣ እናታችን ኾይ ምን እናድርግልሽ? ምንስ እንሁንልሽ? ይሏታል።

ምልክቷን አስቀድመው ይቀድማሉ፣ ያዘዘቻቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ በደስታዋ ይደሰታሉ፣ በድሏ ይኮራሉ፣ በነጻነቷ ይመካሉ፡፡ ለእርሷ የተቀዳውን የመከራ ጽዋ አስቀድመው እነርሱ ይጠጣሉ፣ ለእርሷ የተሳለውን የመከራ ሰይፍ እነርሱ ቀድመው ይመክታሉ፣ እነርሱ እየወደቁ ያኖሯታል፣ እነርሱ እየደከሙ ያበረቷታል፡፡ እርሷን ከሁሉም ያስበልጣሉ፣ እርሷን ከሁሉም አልቀው ይወዳሉ፡፡

አምሳያ የሌላትን እናት አረንጓዴ ካባ አልብሷት፣ ትክ የለሽን እናት የክብር ካባውን ደርቡላት፣ የንግሥና ዘውዷን ድፉላት፣ ጠላት የሚርድበትን፣ የመከራ ቀን የሚታለፍበትን በትረ መንግሥት አስጨብጧት፣ በማያረጅ የልብ ዙፋን ላይ አስቀምጧት፡፡ ያን ጊዜ ዓለም ሁሉ ይደነቅባታል፣ ያን ጊዜ ዓይኖች ሁሉ በስስት ያዩዋታል፡፡

ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውን ትክ የላትም፣ አምሳያም አይግኝላታም፣ ዓለምን ሁሉ ቢያስሷት ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን የምትመሰል ሀገር አያገኙም። ኢትዮጵያን በምንም በማንም አይተኩም፡፡ እርሷ ከሁሉ የተለየች፣ ለዘመናት ጸንታ የኖረች፣ በጠላቶቿ ፊት ግርማና ሞገስን ያገኘች፣ በግፍና በትዕቢት የተነሱባትን ሁሉ በእግሮቿ ሥር የጣለች፣ በወዳጆቿ የተወደደች፣ ተቆጥረው የማይዘለቁ፣ ተዝቀው የማያልቁ ታሪኮችን አቅፋ የያዘች፣ በድል አድራጊነቷ፣ በነጻነቷ፣ በከበረው ሃብቷ የታወቀች ናት፡፡

ቅን ኢትዮጵያዊ ከኾንክ ለኢትዮጵያ መልካም ከሚያስቡት ጋር ተባበር፣ ስለ ኢትዮጵያ በአንድነት አብር፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ለሚመጡብህ ግን ተቆጣ፣ ኢትዮጵያ የአባትና የእናት የአደራ ቃል ኪዳን ያለባት፣ የወገን ደምና አጥንት የተተገበረባት ናትና ኢትዮጵያን አትንኩብኝ በል፡፡

ለእርሷ ደግ የሚያስቡትን ደግፋቸው፣ ለእርሷ መልካም የሚያደርጉትን አይዟችሁ በላቸው፣ እርሷን የሚወዷትን ውደዳቸው፣ እርሷን የሚያከብሩትን አክብራቸው፡፡ እርሷን የሚጠሏትን፣ እርሷን የሚያዋርዷትን፣ ግፍና መከራ የሚያደርሷባትን፣ የእርሷን ታሪክ እና ክብር የማይረዱትን ናቃቸው፣ ክፉ ሃሳባቸውንም በመልካም ሃሳብህ አጥፋባቸው፣ የኢትዮጵያን ክብርና ዝና አሳያቸው፡፡

እርሷ ጠላቶች በተነሱባት ዘመን ሁሉ ልጆቿን ጠርታለች፣ ከአራቱም ንፍቅ አሰባስባለች፣ በልጆቿ ጠንካራ ክንድ ጠላቶቿን መክታለች፣ ክብሯን ሳታስነካ ኖራለች፣ ሊደፍሯት የመጡትን በእግሮቿ ስር ጥላ አፈር ትቢያ አድርጋለች፡፡ እርሷ በሚወዷት ልጆቿ አንድነት ነጻነቷን ጠብቃለች፣ ነጻነትን ላጡም ሰጥታለች፣ የባርነት ካባ ለጠቀለላቸው የብርሃንን ካባ አጎናጽፋለች፡፡

እርሷ በተጣራች ጊዜ ጥልና ጥላቻ ይጠፋሉ፣ አንድነት እና ፍቅር ከፍ ይላሉ፣ በምድሯም ደምቀው ይታያሉ፡፡ እርሷ ስትጠራህ አቤት በላት፣ የእርሷ ጥሪ ለማንም አይደለም ለእርሷ ብቻ ነው፡፡ የእርሷ ጥሪ ለአንድ ወገን፣ ለአንድ ንጉሥም አይደለም፣ ለእርሷ ውበት፣ ለእርሷ ነጻነት፣ ለእርሷ አይደፈሬነት፣ ለእርሷ ልማት ብቻ ነው፡፡ በእርሷ ስም ለመልካም ነገር የጠራህ ያልፋል፣ ታሪክ ግን ይጻፋል፡፡ በብራና ላይ ደምቆ ይኖራል፡፡ እናም ለእናት ጥሪ ተነስ፣ ታሪክ ለማጻፍ በርታ፡፡

“ለምለሚቱ ኢትዮጵያ ብላችሁ የዘፈናችሁልኝ፣ የአሥራ ሦስት ወር ጸጋ ያላት እያላችሁ የተቀኛችሁልኝ፣ ውቢቷ ኢትዮጵያ እያላችሁ ያዜማችሁልኝ ልጆቼ ሆይ ለክብሬ የሚመጥነው፣ ከስሜና ከግብሬ ጋር የተስማማውን ካባ አልብሱኝ፣ አረንጓዴውን መጎናጸፊያ ደርቡልኝ” እያለች ልጆቿን ጠርታለች፡፡

ጥሪዋን ስሟት፣ በዓድዋ ላይ እንደተሰባሰቡት፣ ከዓድዋም አስቀድሞ በአንድነት እንዳበሩት፣ የጣልያንን ወራሪ ድል ለመምታት በአንድነት በዱር በገደል እንደተዋደቁት፣ በካራማራ ላይ ስለ እናት ሀገር ጥሪ እንደተገናኙት፣ በአንድነት ክንዳቸው ሀገር እንዳቆዩት፣ በታላቋ ምድር ታላቅ ታሪክ እንደጻፉት ዛሬም ኢትዮጵያ ለሌላ ተግባር ልጆቿን ጠርታለች፡፡

“ኑ! እና የሚያምርብኝን የተወደደውን ካባ ደርቡብኝ” ብላለች፡፡

ለዘመናት ለምለም ኾና የቆችው ኢትዮጵያ ከዓመታት ወዲህ ውበቷ እየቀነሰ፣ አረንጓዴ ካባዋ እየተገፈፈ ሄዷል፡፡ የደን ሽፋኗም አሽቆልቁሏል፡፡ ይህን የጠወለገ ውበቷን፣ እየተገፈፈ የሄደውን ካባዋን መልሶ ለማልበስ፣ ውበቷንም እንደ ቀደመው አድርጎ ለመመለስ ጥረቶች ከተጀመሩ ቆይቷል፡፡

ዓመታትን በዘለቀው ኢትዮጵያን አረንጓዴ ካባ የማልበስ ዘመቻ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች በኢትዮጵያ ምድር ተፈልተው፣ በኢትዮጵያውያን እጆች በኢትዮጵያ ተተክለዋል፡፡ ብዙዎችም ጸድቀው፣ ለምድሯ መጎናጸፊያ ኾነዋል፡፡ እነኾ ኢትዮጵያ ተጨማሪ መጎናጸፊያ ስላስፈለጋት፣ አረንጓዴ አድርጉኝ፣ ውበቴንም መልሱልኝ ስትል ልጆቿን ጠርታለች፡፡

ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም ደግሞ ልጆቿን በአንድነት ከዳር ዳር የጠራችበት ቀን ናት፡፡ ጀንበር ዘልቃ እስክትጠልቅ ድረስ 500 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ቀጠሮ ተይዟል፡፡ የሀገር ፍቅር፣ የሀገር ክብር፣ ጉልበት እና ተነሳሽነት ላላቸው ሁሉ ጥሪው ቀርቧል፡፡

የታቀደው ሁሉ ከተፈጸመ ኢትዮጵያ በዓለም ፊት አዲስ ታሪክ ታስመዘግባለች፣ የራሷን ክብር ከፍ አድርጋ ትሰቅላለች፡፡ ለዓለም ሁሉ ምሳሌና አርዓያ መኾን ትችላለች፡፡ የታሰበው ሁሉ ከኾነ የሚኮሩት ኢትዮጵያውያን፣ በመልካም ስም የሚጠሩት ኢትዮጵያውያን፣ በዓለም ፊት በክብር የሚታዩት ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡

የጠራችህ፣ ለታሪክና ለክብር ያጨችህ ኢትዮጵያ እንደኾነች ተረዳ፡፡ በማሳህ ችግኞችን ትከል ያንተው ልጆች ከጥላቸው ያርፉባቸዋል፣ ያንተው ልጆች ከፍሬያቸው ቆርጠው ይመገቧቸዋል፡፡ ያንተው ሀገር ኢትዮጵያ ያምርባታል፣ ያንተው ሀገር ኢትዮጵያ ከውበት ላይ ውበት ይጨምርባታል፡፡ ለኢትዮጵያ ከአንተ ውጭ የሚቀርባት፣ ከአንተ በላይ የሚያስብላት፣ ከአንተ በላይ ትዕዛዟን የሚቀበላት እንደሌለ አስብ፡፡ የእርሷ ጥሪ ወደ ሌሎች አትግፋ ለእኔ ነው ብለህ ተቀበል እንጂ፡፡

ተነሱ ኢትዮጵያን ውቡን ካባ አልብሷት፣ የተመረጠውን ስጧት፣ እናቴ ሆይ አለንልሽ በሏት፡፡ ጥሪውም ከኢትዮጵያ ነው፣ እሽታውም ለኢትዮጵያ ነው፣ ስጦታውም ለኢትዮጵያ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሁሉንም ስጧት፡፡ ኢትዮጵያን ከፍ ከፍ አድርጓት፡፡

አምሳያ ለሌላት እናት የተዋበውን አልብሷት፣ ትክ ለሌላት እናት የጠየቀችውን ስጧት፣ ለክብሯ መገለጫ መጎናጸፊያውን ደርቡላት፡፡ በአንድነታችሁ ለዓለም ታዩ፡፡ በአንድነታችሁ ችግኝን ትከሉ።

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የከፍተኛ ትምህርት መውጫ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች ውስጥ 84.7 በመቶ 50% እና ከዚያ በላይ በማምጣት ማለፋቸውን አስታወቀ።
Next article“የኅብረተሰቡን የንጹህ መጠጥ ዉኃ አቅርቦት ሽፋንን ለማሳደግ እየሠራን ነው” የምሥራቅ ጎጃም ዞን ውኃ እና ኢነርጂ መምሪያ