ለሠራተኞች በሚከፈል ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ማነስ ምክንያት የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ልማት ፓርክ ሊዘጋ እንደሚችል ተገለጸ፡፡

224

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 08/2012ዓ.ም (አብመድ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ያለበትን ሁኔታ ለመመልከትና ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኩ የገቡ አምራች ኩባንያዎች አፈጻጸማቸውን በተመለከተ ምልከታ አድርጓል፡፡

ለሰራተኞች በሚከፈል ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ማነስ ምክንያት የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ልማት ፓርክ ሊዘጋ እንደሚችል የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ልማት ፓርክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሕመድ ሰይድ ገልጸዋል፡፡

ፓርኩ 2 ሺህ 147 ሰራተኞችን ያቀፈ ሲሆን ፣ በአንደኛው ሩብ አመት 628 ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ 579 የሚሆኑ ወጣቶች ወደ ስራ መግባታቸው ተገልጿል።

ይሁን እንጂ በደመወዝ ማነስና ተያያዥ ምክንያቶች በሩብ ዓመቱ 526ቱ ፓርኩን ለቅቀው እንደወጡ ኃላፊው አክለዋል፡፡

‹‹የችግሩ አሳሳቢነት ፓርኩን ሊያዘጋው እንደሚችልና በፍጥነት የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ማሻሻያ ይደረግ ብለን ለሚመለከተው አካል ብናሳዉቅም ምላሽ አላገኘንም›› ብለዋል አቶ አህመድ፡፡

ፓርኩ በአንድ ዓመት ከአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ሰባት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚገመት የተለያዩ ምርቶችን ወደ ዉጭ ኤክስፖርት ማድረግ ችሏል፡፡

አንድ ያለቀለት ሙሉ ሱፍ ከኢንዱስትሪ ፓርኩ ሲወጣ ከአምስት እስከ ስምንት የአሜሪካን ዶላር እንደሆነ የገለጹት አቶ አህመድ፣ በዓለም ገበያ ግን ከ 300 እስከ 1700 የአሜሪካን ዶላር እንደሚሸጥ ጠቅሰዋል፡፡

እንዲህ ዓይነት አሠራሮችን ፓርኩን ለከፍተኛ ኪሳራ እየዳረጉት ስለሚገኙ እንዲቆሙ የሚመለከተው አካል ሊሠራበት ይገባል ተብሏል፡፡

የኤክስፖርት አፈጻጸሙ የተሻለ መሆኑ ፣ ኤክፖርት ተኮር ምርቶች መመረታቸው፣ የፓርኩን ደኅንነት ለመጠበቅ ጥብቅ ክትትል መደረጉ፣ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋራ ሥራዎች በጋራ እየተሠሩ መሆናቸውን ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ከገለጻቸው መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ቋሚ ኮሚቴ የቴክኖሎጂ ዕውቀት ሽግግር፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ አነስተኛ መሆኑ፣ የሠራተኞች የቤት ግንባታ መጓተትን በትኩረት ሊሠራባቸው እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡ የሥራ ኃላፊዎቹ በበኩላቸው በቋሚ ኮሚቴው በኩል የተገለጹላቸውን አስተያየቶች ተቀብለው በትኩረት እንደሚሠሩባቸው ተናግረዋል፡፡

ምንጭ፡-የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

Previous articleየአማራ ክልል የሥራ ኃላፊዎች በክልሉ ኢንቨስትመንት እና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ሲያትል ገቡ፡፡
Next articleበናይል ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አቋሞችን መከተል አለባት?