ሐምሌ 10 /2015 ዓ.ም ለሚካሄደው የአረንጎዴ አሻራ ልማት መርሐ ግብር የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማጠናቀቁን የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

41

ገንዳ ውኃ: ሐምሌ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም በሀገር ደረጃ ለሚካሄደው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሐ ግብር የቅድመ ዝግጅት ተግባር ማጠናቀቁን አስታውቋል።

ዞኑ በ2015/2016 በጀት ዓመት በሥነ ሕይወታዊና በደን አግሮ ፎረስተሪ ከ1 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል አቅዶ እስካሁን በቆጠራ የተረጋገጠ 670 ሺህ በላይ ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን በመምሪያው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ቡድን መሪ ፈንታሁን ፍስሐ ተናግረዋል።

እንደ ቡድን መሪው ገለጻ በአንድ ቀን አረንጓዴ አሻራ ልማት መርሐ ግብር በዞኑ በሚገኙ አራት ወረዳዎች ከ44 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል ጉድጓዶች ተዘጋጅተዋል።

ለችግኝ ተከላው ከ16ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተለይቷል።

በተከላ መርሐ ግብሩም ከ4ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ።

የሚተከሉት ችግኞች የአካባቢውን ሥነ ምህዳር ከማስጠበቅና ምርታማነትን ከመጨመር ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ናቸው።

ከእነዚህ ውስጥም እንደ አካሻ ሴኔጋል፣ ሽመል፣ ማንጎና ሚም ተጠቃሽ ናቸው።

የዞኑ የደን ሽፋን 34 በመቶ መኾኑን የገለጹት አቶ ፈንታሁን ሽፋኑን በ0 ነጥብ 5 በመቶ ከፍ ለማድረግ ችግኞችን ከማፍላትና የተከላ ቦታዎችን በጅፒኤስ ከመከለል በተጨማሪ የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ ጥበቃ እየተደረገላቸው መኾኑንም ተናግረዋል።

ምዕራብ ጎንደር ዞን ከ624 ሺህ በላይ የሚኾነው መሬት በደን የተሸፈነ ሲኾን የአልጣሽ ፣ የጎደቤ ብሔራዊ ፓርክ እና የማኅበረሥላሴ አንድነት ገዳም ጥብቅ ደን ሰፊውን በታ ይይዛሉ ተብሏል።

ዞኑ መትከል ላይ ብቻ ሳይኾን ነባር የደን ቦታዎችን ከልሎ መጠበቅና መንከባከብ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መኾኑንም ቡድን መሪው ገልጸዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሚሳተፉ የዞኑ ነዋሪዎችም በባለፈው ዓመት ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ጸድቀው አገልግሎት እንዲሰጡ፤ ጉዳት እንዳይደርስባቸው በመጥበቅ፣ ውኃ በማጠጣት፣ በመኮትኮትና በመንከባከብ ኀላፊነታቸውን መወጣታቸውን ለአሚኮ ገልጸዋል።

በዚህ ዓመትም የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ መዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት።

ባለፈው ዓመት ከተተከሉት 418 ሺህ ችግኞች 69 በመቶ መጽደቃቸውን ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አስፈጻሚ ተቋማት አካቶ ትግበራን በልኩ ተፈጻሚ እንዲያደርጉ ኀላፊነታችንን እንወጣለን” ወይዘሮ አበራሽ ታደሰ
Next article“መንግሥት አማራ ነን እንጅ አማራ እንሁን አላልንም እያልን በተደጋጋሚ ለምንጠይቀው የማንነት ጥያቄ ሕጋዊ እውቅና ሊሰጠን ይገባል” የማይጠብሪ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች