በናይል ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አቋሞችን መከተል አለባት?

268

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 08/2012ዓ.ም (አብመድ) አቶ ዘውዱ መንገሻ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህርና ተመራማሪ ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሕግ፣ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በዓለማቀፍ ሕግ ተከታትለዋል፡፡ በወሰን ተሻጋሪ ወንዞችና አጠቃቀማቸው ዙሪያ ተደጋጋሚ ጥናቶችን ሠርተዋል፡፡
በግንባታ ላይ ከሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን መካከል እየተካሄዱ ያሉ ድርድሮችን አስመልክቶ ኢትዮጵያ ማድረግ የሚገባትን ጥንቃቄና መወሰድ ያለባቸውን የመደራደሪያ አቋሞች አስመልክቶ በተለይም ከግብጽ ተለዋዋጭ አቋም ጋር በማያያዝ ሙያዊ ትንተና የያዘ ጽሑፍ አድርሰውናል፤ ቀጥሎ ቀርቧል፡፡

ኢትዮጵያ በታለቁ የሕዳሴው ግድብ ድርድር ሂደት ምን ማድረግ ይገባት ይሆን?

ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የምሥራቅ ናይል ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት በተለይም በኢትዮጵያና የታችኛው የናይል ወንዝ ተፋሰስ ሀገር ከሆነችው ግብፅ ጋር አለመግባባቶቹ ተካርረው ተስተውለዋል፡፡ በመሠረቱ የወንዙ አጠቃቅም ሁለቱን ሀገራት ለረዥም ጊዜ ሲያጨቃጭቅ የቆየ ቢሆንም በተለይም የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት መጋቢት 2003ዓ.ም ጀምሮ አንድ ጊዜ ከረር ሌላ ጊዜ ረገብ እያለ እስከ ዛሬ ድረስ ቀጥሏል፡፡

ግብፅ ለረጅም ዘመናት ወንዙን የመጠቀም ዕድል አስቀድሞ አግኝታ ቆይታለች፡፡ በተለይም ደግሞ ግብፅ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ከነበረችበት ወቅት አካባቢ አንስቶ በወንዙ ላይ ሰፊ የእርሻ እና ሌሎች የልማት ተግባራት ተሰማርታለች፡፡ እንግሊዝ የቅኝ ግዛት በያዘችበት ወቅትም ሆነ ግብፅ ነፃነቷን ከተጎናፀፈች በኋላ የዚህን ወንዝ አጠቃቅም በተመለከተ የተለያዩ ስምምነቶች የተደረጉ ቢሆንም ሁሉም የላይኛውን ተፋሰስ ሀገራት ጥቅም ከግምት ውስጥ ያላስገቡና ያልተሳተፉባቸው ነበሩ፡፡ ግብፅም እነዚህ የላይኞቹን የተፋሰስ ሀገራት በማግለል በቅኝ ግዛት ዘመንና ከቅኝ ግዛት ማግስት የተደረጉ ስምምነቶች ተግባራዊ እየሆኑ እንዲቀጥሉ ትፈልጋለች፤ ለዚህም ስምምነቶቹ በምንም ዓይነት ሁኔታ ሊገዟቸው የማይገቡ ሀገራትን በተለይም ኢትዮጵያን እነዚህን ስምምነቶቹን እንድታከብር ስትወተውትና ኢትዮጵያውንና ዓለማቀፉን ማኅበረሰብ ጭምር ስታደናግር ይስተዋላል፡፡

አብዛኞቹ ስለዓለም አቀፍ ወንዞች ሕግ የጻፉ የዘርፉ ልሂቃን እንደሚሉት ከሆነ የዓለም አቀፍ (ድንበር ተሻጋሪ) ወንዞችን የተፋሰስ ሀገራት በወንዞቹ ሲጠቀሙ በትብብር መንፈስ ሊሆን እንደሚገባ ይመክራሉ፤ በትብብር መንፈስ መጠቀሙም ለተፋሰስ ሀገራት በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባባዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሚያስገኝ በጉልህ ያስረዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ በናይል ወንዝ አጠቃቅም ዙሪያ ለዘመናት የነበረው የታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት የብቸኝነትና ቀዳሚ ተጠቃሚነት ጉዳይ (በተለይ በግብፅ) ትርጉም ባለው መልኩ ወንዙን ሁሉም የተፋሰስ ሀገራት ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እንቅፋት ፈጥሮ ቆይቷል፡፡

ግብፅ ከነበራት ቀጠናዊ የፖለቲካ ተፅዕኖ ፈጣሪነት አንፃር በተለያዩ የልማት አጋር ተቋማትና ለጋሽ ሀገራት ላይ በምታደረሰው ጫና እና በሌሎች ሀገራዊ ችግሮች ምክንያት ለዘመናት የላይኞቹ ተፋሰስ ሀገራት በወንዙ ላይ ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ዕድገት ጠቃሚ የሆኑ ተግባራትን (ፕሮጀክቶቹን) እንዳይከወኑ መሰናክል ሆኖባቸው ቆይቷል፡፡ በተለይም በአንዳንድ የናይል ተፈሳሰስ ሀገራት የሚገነቡ አንዳንድ ፕሮጀክቶች በግብፅ ይሁኝታ አግኝተውና በግብፅ መሐንዲሶች ቁጥጥር ሥር ሆነው (የተፋሰሱ ሀገራት ሉዓለዊነታቸውን አሳልፈው ሰጥተው) ሲከውኑ ጭምር ተስተውሏል (እንደዚህ ዓይነት አካሄድ የሀገራትን ሉዓላዊነት የሚደፍር መሆኑን ልብ ይሏል)፡፡

ግብፅ በተደጋጋሚ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግደብ የፕሮጀክት ሐሳብ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ግድቡ እንዳይገነባ የተለያዩ ጥረቶችን ስታደርግ መቆየቷ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵውያን የማይበገር ጥረት ፐሮጀክቱ እውን እንደሚሆን እርግጠኛ መሆናቸውን ተከትሎ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የውኃ አሞላል እንዲሁም ሥራ በሚጀምርበት ወቅት ግብፅ ከዚህ ቀደም ከወንዙ የምታገኘው ጥቅም በምንም ሁኔታ እንዳይነካ ከፍተኛ ጥረት ወደማድረጉ ተግባር መዞራቸውን ድርጊቶቻቸው እያመላከቱ ነው፡፡

ለዓመታት የተደረገው የሀገራቱ ድርድር እና ውይይት ‹‹ውጤት አልባ ነው›› የሚለውን የግብፅ ሹማምንት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሰጧቸውን መግለጫዎች ተከትሎ ጉዳዩ ከረር ብሎ የቆየ ቢሆንም እንደገና የአሜሪካ መንግሥት ባደረገው ጥሪ አማካኝነት የምሥራቅ ናይል ተፋሰስ ሀገራት ማለትም ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን ለረጅም ጊዜያት በውይይት ይዘውት የነበረውን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና የግድቡ ተግባራዊ አሠራር (Operation) ላይ መፍትሔ ለመስጠት ውይይት መጀመራቸውና እስከ ተያዘው ታኅሳስ ወር መጨረሻ ድረስ ለጉዳዩ መፍትሐየ ለመስጠት ስምምነት አድርገዋል፡፡ እስካሁን ድረስ ሁለት ውይይቶች በተፋሰስ ሀገራቱ የተደረጉ ቢሆንም አመርቂ ሊባል የሚችል ውጤት እንዳልተመዘገበ እየተነገረ ነው፡፡ በአጠቃላይ በዚህ የውይይት ሂደትና ድርድር ኢትዮጵያ ልታደርጋቸው የሚገቡ ተግባራትና ጥንቃቄዎች ምን ሊሆኑ ይገባል? የሚለው ጥያቄ ወሳኝ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የተወሰኑ መሠረታዊ ምሁራዊ ዕይዎችን ማጋራት አስፈላጊ ነው፡፡

ለረዥም ጊዜ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ በዲፕሎማትነት የሠሩ ግለሰብ በአንድ ወቅት እንዳወጉኝ ከሆነ የግብፅ ዲፕሎማቶች ሊጨበጥ የሚችል ባሕሪ የተላበሱ አይደሉም፡፡ መልካም አቀራርብ ያላቸውና ጥሩ ጓደኛ መስለው የሚታዩ ቢሆንም የናይልን ጉዳይ ወደ ሀገር ደኅንነት (ኅልውና) ደረጃ ያደረሱት በመሆኑ በሙያተኛ ደረጃ ሙያንና የሙያ ሐሳቦችን መሠረት ባደረገ መልኩ ብቻ መነጋገር የሚችሉ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ከዲፕሎማቶቹና ከባለሙያዎቹ በመነጋገር ጉዳዩን ‹‹ይፈታል›› ብሎ ማመን ተገቢ አይሆን፡፡ የግብፅ ዲፕሎማቶች የሚሰጧቸውን መረጃዎች በጥንቃቄ በማየት ኢትዮጵያ ልታገኝ የምታስበውን መሠረታዊ ጥቅም እንዳታጣ ጥንቃቄ ማድረግም ይገባል፡፡

ግብፆች በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙኃኖቻቸው እንደሚሉት በተለያየ መንገድ በማወዛገብ ከዚህ ቀደም በ1929 እና 1959 (እ.አ.አ) ስምምነቶች የተሰጣትን 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውኃ የማግኘት መብት ኢትዮጵያ ዕውቅና እንድትስጥ እየሞከሩ ነው፡፡ በተለይም የተለያየ ስያሜ እየሰጡ ‹‹የተፈጥሮ መብት፣ የግብፅ የውኃ ድርሻ መብት፣ ታሪካዊ መብት›› እያሉ አንድን ፍላጎት ብዙ ስም በመስጠት ኢትዮጵያ ዕውቅናና ይሁንታ እንድትሰጥበት ለማድረግ እየሞከሩ ነው፤ ስለዚህ ላለመደናገርና የኢትዮጵያን ጥቅም ላለማሳጠት መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡

ግብፅ ከናይል ውጭ ሌላ ምንም የውኃ አማራጭ እንደሌላት የሚነገረው ልማዳዊ ገለጻ ለረዥም ጊዜ በዲፕሎማሲው ተጠቃሚ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ይህ ደግሞ በተቃራኒው ኢትዮጵያ እንድትጎዳ አድርጓል፡፡ ስለሆነም በሚገኘው አጋጣሚ ሁሉ ግብፅ ከናይል ውጭ ብዙ የውኃ አማራጭ እንዳላት በተለይም ከፍተኛ የከርሰ ምድር ውኃ ክምችት ያላት መሆኑንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጀመሩት ጨዋማ ውኃን በማከም ጥቅም ላይ የማዋል ቴክኖሎጂ ውጤታማ እንደሆነ መሞገት ይገባል፡፡ ስለሆነም እነዚህን አብነቶች በማንሳት ለዓለማቀፉ ማኅበረሰብም ግብፅ አማራጭ የውኃ ምንጮች እንዳሏት ማስገንዘብ ይጠበቅብናል፡፡
ሌላው መሠረታዊ ጉዳይ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ውኃ አያያዝና አሠራርን ከግብፁ የአስዋን ግድብ ጋር ለማያያዝ የሚጥሩትን ነገር በአግባቡ መታገልን የሚመለከት ነው፡፡ በተለይም ይህ ግድብ ሲገነባ የየትኛውንም የላይኛውን ተፋሰስ ሀገራት ሳያማክሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ‹‹የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሊት ሂደት የአስዋንን ግድብ መሠረት ባደረገ መልኩ ይደረግ›› የሚለው የግብፅ ሐሳብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚደፍር ከመሆኑ ባለፈ ያረጀውን ‹‹በታች ያሉ የተፋሰስ ሀገራት ያልተቆራረጠ ውኃ የማግኘት መብት አላቸው›› የሚል ቀኖና (የሀርሞን ቀኖና) የሚያስቀጥል እሳቤ ነው፡፡ በተለይም ግልፅ ባልሆኑ የድርድር መስመሮች የአስዋን ግድብን ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ውኃ አሞላል ጋር ለማያያዝ የሚደረገው የግብፅ ጥረት የኢትዮጵያን መሠረታዊ በወንዙ ላይ የመጠቀም መብቶችን የመገደብ ውጤት ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ይህንን የግብፅ ጥያቄ እንደ ትልቅ ቀይ መስመር ማለፍ ልታየውና ልትታገለው የሚገባ ነገር ነው፡፡

ግብፅ በዚህ ወቅት ከኢትዮጵያ በንፅፅር የተሻለ የሚመስውን ውስጣዊና ሀገራዊ መረጋጋት በመጠቀም ኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር እንደምትጥር መገንዘብ ይገባል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ይህንን ጉዳይ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተገቢና አሳማኝ ትንተና ማቅረብ የሚችሉ ባለሙያዎችን ወደ ፊት በማውጣት ማስረጃ የመስጠት ሥራ ለነገ የሚባል መሆን የለበትም፡፡

ግብፆች ለረዥም ጊዜያት በናይል አጠቃቅም ላይ የነበራቸውን ተጠቃሚነት ለማስቀጠል ለዘመናት የላይኞቹን የተፋሰስ ሀገራት ተጠቃሚ ያላደረጉ ‹‹የትብብር ማዕቀፎች›› ሲያደርጉ እንደነበር ይታወሳል፡፡ አሁንም በኢትዮጵያ በኩል የግድቡ ግንባታ ሥራ በተገቢው ሁኔታ እንዳቀጥል ለማድረግ ለዘመናት ሲያደርጉት እንደነበረው ሁሉ ትርጉም አልባ ድርድሮችን ከኢትዮጵያ ጋር በማድረግ ጊዜ ለመግዛት እንደሚሞክሩ መረዳትና አለመዘናጋት ይገባል፡፡

ጉዳዩ ወደ 3ኛ አደራዳሪ ወገኖች የማይሄድበትን ሁኔታ መፍጠርም ከኢትዩጵያ የሚጠበቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የግድ ጉዳዩ በ2015 (እ.አ.አ) በተፈረመው የመግባቢያ መርሆች አንቀፅ 10 መሠረት ወደ አደራዳሪ 3ኛ ወገን የሚያመራ ከሆነም በዚህ ሂደት የሚመረጡት አደራዳሪዎች ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ በተለይም የአደራዳሪዎቹ ሚና በተገቢው ሁኔታ የሚገደብብበትን አማረጭም መፈለግ ይገባል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ተገቢውን ማስረጃ በማደራጀት በድርድሩ ሂደት የሚሳተፉ ዲፕሎማቶችን የሚደግፉ የዘርፉ ባለሙያዎችን ማደራጀት አሁንም በትኩረት ሊሠራበት የሚገባ እጅግ አስቸኳይ ተግባር ነው፡፡

በሌላ በኩል አስገዳጅ ወደ ሆኑ የግጭት መፍቻ መንገዶች ማለትም ወደ ዓለማቀፍ ፍርድ ቤትና ዳኝነት ሰጭዎች መሄድ ግን በፍፁም ሊታሰብ አይገባም፡፡ አበው እንደሚሉት «እጀግ ብልጥ ሰው ከሌላው ሰው ስህተት ይማራል፤ ብልጥ ሰው ደግሞ ከራሱ ስህተት መማር ይኖርበታል» እንደሚባለው ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ከሠራችው ስህተት ልትማር ይገባል፡፡

ከዚህ ባሸገርም ጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ አህመድ (ዶክተር) በዚህ ወቅት ያላቸውን ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪነት በመጠቀም በተለይ የተፋሰሱ ሦስት ሀገራት ብቻ ያጽደቁትን የጋራ ተጠቃሚነት የስምምነት ማዕቀፍ ሌሎች ሀገራት እንዲፈርሙና እንዲያጸድቁ በማበረታታት ከፕሮጀክት ስምምነቱ በተጨማሪ በናይል ወንዝ ላይ ያለውን የፍትሐዊነትና በእኩልነት የመጠቀም ሁኔታ እንዲሰፍን መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡ የዚህ ስምምነት ዋና ተዋናይ ኢትዮጵያ ሆና የተፋሰሱ ሀገራት ‹‹በናይል ወንዝ ላይ በፍትሐዊነትና በእኩልነት መጠቀም አለብን›› የሚል የተሟሟቀ ስሜት እንዲኖራቸው ለማድረግ መቀስቀስም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ከሆነ ኢትዮጵያ ብቻዋን ሳትሆን ሌሎቹንም ያካተተ ሆኖ ግብፅ የነበራትን ወንዙን በብቸኝነት የመጠቀም ሁኔታ መሞገት ያስችላል፡፡

የኢትዮጵያን የመልማት መብት ግልፅ በሆነ ደረጃ ማሳየትም አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በልዩ ሁኔታ በተፋሰሱ ውስጥ ያሉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ያሉበትን የኑሮ ሁኔታ በአግባቡ በማደራጀት የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ እንዲያውቅ ማድረግም ይገባል፡፡ በተለይም ለዘመናት በነበረው ወደ አንድ ወገን ያጋደለ ጂኦፖለቲካዊ እሳቤ ምክንያት ከ86 በመቶ በላይ የሚሆነው የናይል ወንዝ ውኃ ከኢትዮጵያ እየተገኘ ሳለ ከዚህ የውኃ አካል ተገቢውን ጥቅም እንዳላገኘች ማሳዬት፡፡ በአንጻሩ ግብፆች ይህንን ውኃ ከተፋሰሱ ውጭ በማውጣት በሲናይ በረሃ ጭምር በመውሰድ እየተጠቀመችበት እንደሆነና፤ በኢትዮጵያ ግን ከ80 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ኤሌክትሪክ የማያገኝ እንደሆነና የምግብ ዋስትናውንም እንዳላረጋገጠ፣ ከ25 ከመቶ በላይ ሕዝባችንም ከድህነት ወለል በታች እንደሆነ ማሳወቅና የእነዚህን ዜጎች ሕይወት ለማሻሻል የግድ ውኃንን መጠቀም እንዳለብን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስገንዘብ ይገባል፡፡

ከዚህ ቀደም የደረጉ ስምምነቶች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የታችኞቹን የተፋሰስ ሀገራት ጥቅም እንጂ የላይኞቹን ጥቅም በፍፁም ከግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑን በግልፅ ማስረዳትም አስፈላጊ ነው፡፡

Previous articleለሠራተኞች በሚከፈል ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ማነስ ምክንያት የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ልማት ፓርክ ሊዘጋ እንደሚችል ተገለጸ፡፡
Next articleየጥምቀት በዓል በዓለም ቅርስነት መመዝገብ ክዋኔውን ለቀጣይ ትውልድ ጠብቆ ከማስተላለፍ ባሻገር የኢኮኖሚ ተጠቃነሚትን እንደሚያሳደግ ተገለጸ::