
ባሕር ዳር: ሐምሌ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ልዩ ድጋፍ ለሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች አስፈጻሚ ተቋማት አካቶ ትግበራን በልኩ ተፈጻሚ እንዲደርጉ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ለአማራ ክልል ምክር ቤት ሴቶች ፎረም አባላት ሥልጠና ተሰጥቷል።
ሥልጠናው በየደረጃው ያሉ የምክር ቤት አባላት በሥርዓተ ፆታ፣ በሕጻናት፣ በአካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ላይ አስፈጻሚ ተቋማት በተቀመጠው ሕግና ደንብ መሠረት ተልዕኳቸውን እንዲወጡ በክትትልና ቁጥጥር ተግባራቸው ማረጋገጥ የሚያስችል ነው ተብሏል።
ለምክር ቤት አባላቱ ሥልጠናውን የሰጡት የሴቶች ፣ ህጻናትና ማኀበራዊ ጉዳይ ቢሮ የአካቶ ትግበራ ከፍተኛ ባለሙያ ሰለሞን ክንዱ እንዳሉት አስፈጻሚ ተቋማት አካቶ ትግበራን በሚፈለገው ልክ እየፈጸሙት አይደለም።
ቢሮው ለአስፈጻሚ ተቋማቱ የአካቶ ትግበራ ማስፈጸሚያ ስልት አዘጋጅቷል ያሉት አቶ ሰለሞን በየደረጃው ያሉ የምክር ቤት አባላቱም በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ክትትልና ቁጥጥር እንዲያደርጉ የሚያስችል ግንዛቤ ፈጠራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
አስፈጻሚ ተቋማቱ ልዩ ድጋፍ የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መብታቸውን የማስከበር፣ ጥቅማቸውንም የማረጋገጥ ክፍተቱ የጎላ ነው ብለዋል።
በተቋማት የአካቶ ትግበራው ስኬታማ እንዳይኾን ያደረገው የአመራር ቁርጠኝነት አለመኖር፣ የግንዛቤ ክፍተት፣ በማይተገብሩ ተቋማት ላይ ተጠያቂነት አለመኖር መሰረታዊ ችግር ኾኗል ነው ያሉት አቶ ሰለሞን።
በየደረጃው ያሉ የምክር ቤት አባላት ጉዳዩን ተረድተው ለተፈጻሚነቱ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
ወይዘሮ አበራሽ ታደሰ በአማራ ክልል ምክር ቤት የሰው ሀብትና ቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው። በጉዳዩ ላይ ለአሚኮ እንዳሉት የምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አካቶ ትግበራን በተሰጠው ኀላፊነት ልክ ተግባራዊ የማያደርግን፣ እንደ ሥራም ወስዶ አቅዶ የማይፈጽም አስፈጻሚ ተቋም ላይ የተሰጠንን ሥልጣንና ተግባር እንጠቀማለን ብለዋል።
ሕግ ማውጣት፣ መቆጣጠርና ውክልናን በአግባቡ መወጣት የምክር ቤቶች ኀላፊነት ነው ያሉት ወይዘሮ አበራሽ በቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በሚደረግ ክትትልና ቁጥጥር አካቶ ትግበራን በአግባቡ ተፈጻሚ የማያደርግን ተቋም ለምክር ቤቱ እናቀርባለን ብለዋል።
ባለፈው በነበረው የቋሚ ኮሚቴ ግምገማም አካቶ ትግበራን ተፈጻሚ የማያደርጉ ተቋማት ሪፖርታቸውንም ለምክር ቤቱ እንዳያቀርቡ እስከ ማድረግ የደረሰ እርምጃ እንደሚወሰድ ተግባብተናል ነው ያሉት።
እስከ አሁን ባለው የቋሚ ኮሚቴ ግምገማ አካቶ ትግበራን ተቋማቱ እንደግዴታ አለመውሰድ፣ እንደ ኀላፊነት እና እንደ ሥራም ቆጥሮ አለመተግበር ታይቶባቸዋል ብለዋል። እናም “አስፈጻሚ ተቋማት አካቶ ትግበራን በልኩ ተፈጻሚ እንዲያደርጉ ኀላፊነታችን እንወጣለን” ነው ያሉት ወይዘሮ አበራሽ ታደሰ።
የሥልጠናው ተሳታፊዎችም ሥልጠናው ጥሩ ነው፤ ዛሬም እንደ ትናንቱ ስለ አካቶ ትግባራ የሚሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ መልካም ነው፤ ነገር ግን ከመሠልጠን ባሻገር የተግባር ሰዎች መኾን አለብን ብለዋል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!