
ደብረታቦር: ሐምሌ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ”ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ መልዕክት ለሚከናወነው የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ 224 ሚሊዮን ችግኞችን ማዘጋጀቱን የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪ ገልጿል፡፡
28 ነጥብ 4 ሚሊዮኑ በአንድ ቀን ተከላ ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም እንደሚተከል የገለጹት የመምሪያው ምክትል ኀላፊ ቻላቸው እንግዳው ናቸው።
ኀላፊው 26 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 207 ሚሊዮን የችግኝ መትከያ ጉድጓድ መዘጋጀቱንም ነው የተናገሩት፡፡
የግብርና መምሪያው ምክትል ኀላፊ በተለይም ለአሚኮ በሰጡት መረጃ፦
🌳 ለተከላው 14 ወረዳዎች በ229 ቀበሌዎች ውስጥ 464 ተፋሰሶች ተዘጋጅተዋል፡፡
🌳 568 ሺህ 184 የሰው ኀይል እንደሚሳተፍበትም ይጠበቃል።
🌳 የዘንድሮው ተከላ በዋናነት ለአፈርና ውኃ ጥበቃ፣ ለደን ልማትና ለጥምር እርሻ ዓላማ እንደሚውልም ነው አቶ ቻላቸው የገለጹት፡፡
ዘንድሮ በዞኑ ከሚተከለው ውስጥ 2 ሚሊዮን የሚኾኑት የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች መኾናቸው ታውቋል፡፡
በየደረጃው የሚገኘው የግብርና መዋቅርና አመራሩ ከሕዝቡ ጋር የንቅናቄ መድረክ ውይይት ማድረጉንና ለዘንድሮ የችግኝ ተከላ ሥኬት መግባባት ላይ መደረሱም ነው የተብራራው፡፡
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!