
ባሕር ዳር: ሐምሌ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሚተከለው ችግኝ እንዲጸድቅ ትክክለኛውን የአተካከል ዘዴ መከተል እንደሚገባ በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የደን ልማት ባለሙያው አቶ ደመላሽ አምሳሉ ተናግረዋል። በችግኝ ተከላ ወቅት ተክሉ እንዳይጸድቅ የሚያደርጉ ልማዳዊ አሠራሮችን ማስወገድ እንደሚገባም ባለሙያው አንስተዋል።
እንደ ባለሙያው ገለጻ ተቆፍረው በመቆየታቸው ውኃ ያቆሩ ጉድጓዶች ውስጥ ችግኝ መትከል አግባብ አይደለም። ምክንያቱም የችግኙ ሥር በቀጥታ ውኃ ስለሚያገኘው ይበሰብስና ይደርቃል።
ሌላው ለችግኝ መድረቅ መንስዔ የሚኾነው በረግረጋማ ቦታዎች ላይ መትከል ነው። በነዚህ ቦታዎች ላይ በቀጥታ ችግኝ ከመትከል ይልቅ ቅድሚያ ተፋሰስ በመሥራት ማንጣፈፍ እንደሚገባ አቶ አምሳሉ ተናግረዋል።
በቂ ውኃ መቋጠር በማይችሉ ተራራማ ቦታዎች ላይ መትከልም በችግኙ ጽድቀት ላይ አሉታዊ ጎን አለው። በእንዲህ አይነት ቦታዎች ላይ ችግኝ ከመትከል በፊት መሬቱን እርጥበት ማስቋጠር የሚችል የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ቀድሞ ማከናወን እንደሚገባ ባለሙያው ጠቁመዋል።
የተተከለ ችግኝ ለመጽደቅ የተመጣጠነ እርጥበትን እንደሚፈልግ ነው ባለሙያው የመከሩት። “ችግኝ የምንተክልበት ቦታ ከመጠን ያለፈ ወይም ያነሰ እርጥበት ካለው ችግኙ አይጸድቅም” ነው ያሉት አቶ ደመላሽ
የሚተከሉ ችግኞች በብዛት ጸድቀው የደን ሽፋናችንን ለማሳደግ እና እውነትም ታሪክ ለመሥራት ከጉድጓድ ቁፋሮ ጀምሮ ትክክለኛውን የችግኝ ተከላ መንገድ መከተል ይገባል ሲሉም አቶ ደመላሽ መክረዋል።
እንደ ባለሙያው ምክረ ሃባብ:-
👉የመትከያ ጉድጓዱ 30 ሴንቲ ሜትር ጥልቀት መኾን አለበት
👉የጉድጓዱ አፈር በሚወጣበት ጊዜ ከላይ የወጣው አንድ ቦታ፣ ከወደውስጥ የሚወጣው ደግሞ ሌላ ቦታ መቀመጥ አለበት
👉 የሚተከለው ችግኝ በፕላስቲክ የተፈላ ከኾነ በተከላ ወቅት ይቀደድና ፕላስቲኩ እስካረፈበት የላይኛው ጫፍ ድረስ በጉድጓዱ መሸፈን አለበት
👉 የችግኙ ስር ከፕላስቲኩ የታችኛው ወለል በታች ዘልቆ ያደገ ከኾነ በመቀስ ተቆርጦ መተከል አለበት
👉 በተተከለው ችግኝ ላይ አፈር ሲመለስ ከወደ ላይ የወጣው አፈር መጀመሪያ ይመለስና ጉድጓዱን ስንቆፍር ከወደውስጥ አውጥተን ለብቻ ያስቀመጥነውን አፈር ከላይ ማልበስ ያስፈልጋል።
👉ወደተተከለው ችግኝ ስር ውኃ እንዳይገባ ለመከላከል የመለስነውን አፈር በትንሹ ጫን ጫን በማድረግ ማያያዝ ይመከራል
በዚህ መልኩ የተተከለ ችግኝ የመጽደቅ እድሉ የሰፋ እንደኾነ የገለጹልን ባለሙያው ከተተከለ ከሁለት ወር በኋላ መኮትኮት እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!