“መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጠዋት 12፡00 ጀምሮ እስከ ምሽት 12፡00 ድረስ አሻራውን በኢትዮጵያ ካርታ ላይ ያሳርፍ” ግርማ አመንቴ (ዶ.ር)

53

ባሕር ዳር: ሐምሌ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ነገን ዛሬ እንትከል በሚል መርህ በቀን 500 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ቀጠሮ ይዛለች፡፡ ቀጠሮ የተቆረጠላት ቀንም ነገ ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም ናት፡፡

በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የተያዘውን እቅድ አስመልክተው ማብራሪያ የሰጡት የግብርና ሚኒሰትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል መርሃ ግብር ዝግጅቱ ተጠናቋል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ አራቱም ንፍቅ በአንድ ጀንበር የሚተከሉ ችግኞች ሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር ባዘጋጀው ሶፍትዌር መሰረት በአንድ ማዕከል ተሰባስቦ ለዓለም ሁሉ ይገለጻል ነው የተባለው፡፡

የነገው ችግኝ ተከላ ለዓለም ስጋት የሆነውን የአየር ንብረት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ምላሽ እየሰጡ መሆናቸውን በአንድ ጊዜ የሚያሰሙበት ነው ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት ለዓለም ሁሉ የሚታዩበትና የሚያሳዩበት መሆኑንም አንስተዋል፡፡ አበው ትናንት በዓድዋ ላይ ተባብረው ያስመዘገቡትን ድል፣ እንደገናም በሕዳሴ ግድብ አንድ ላይ በመተባበር ኢትዮጵያውያን ያለማንም አጋዥ ያስመዘገብነውን ድል፣ አሁን ደግሞ በአረንጓዴ አሻራ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢ ኢትዮጵያውያን አንድ ላይ ሆነው አዲስ ድል መጻፍ እንደሚችሉ የሚያሳዩበት አዲስ ቀን ነውም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዲጅታል ቴክኖሎጂ የደረሰችበትን አቅም ያሳየ፣ ከሁሉም ኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚተከሉ ችግኞች ወደ አንድ ቋት መጥተው ለዓለም የሚታዩበት መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ ይህም ቀኑ ከችግኝ ተከላ በላይ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስተባበሪነት፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር፣ የስፔስ ሳይንስ ኢንስቲትዩት፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ኢንሳ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ተቋማት በመተባበር ዝግታችንን አጠናቀናል ነው ያሉት፡፡ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጠዋት 12፡00 ጀምሮ እስከ ምሽት 12፡00 ድረስ አሻራውን በኢትዮጵያ ካርታ ላይ እንዲያሳርፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ነገ የሚተከሉ ችግኞች ተክለን ብቻ ዘወር የምን ሳይሆን የተተከሉትን ችግኞች እንክብካቤ ማስቀጠል አለብን ነው ያሉት፡፡ ነገ የሚተከሉት ችግኞች ዓለም በሙሉ የሚከታታላቸው ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያውያን ተክለን፣ ተንከባክበንና አሳድገን ለዓለም ማሳየት አለብንም ብለዋል፡፡

በራሳችን የያዝነውን ክብረ ወሰን ራሳችን በማሻሻል ሌላ ታሪክ እንሥራ ብለዋል ሚኒስትሩ በመልእክታቸው፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለሐምሌ 10/2015 ዓ.ም የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ ዝግጅት መጠናቀቁን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ገለጸ።
Next article“ችግኝ የምንተክልበት ቦታ ከመጠን ያለፈ ወይም ያነሰ እርጥበት ካለው ችግኙ አይጸድቅም” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ