የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብርን ስኬታማ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማጠናቀቁን የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

39

ደሴ: ሐምሌ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በዞኑ በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ላይ ከ48 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ይተከላሉ።

በአማራ ክልል በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር 260 ሚሊዮን ችግኞች በ26 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እንደሚተከሉ ተገልጿል።

የዚሁ አካል የኾነው በደቡብ ወሎ ዞንም ነገ 48 ሚሊዮን 738 ሺህ ችግኞች በ4 ሺህ 873 ሄክታር መሬት ላይ ይተከላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ለሥራው ስኬታማነትም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቅቀዋል። በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ከ230 ሚሊዮን በላይ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች መቆፈራቸውን የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ አሕመድ ጋሎ ተናግረዋል።

በዕለቱ የሚተከሉ ችግኞችም ወደ ተከላ ቦታ የማጓጓዝ ሥራም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው።

ችግኞች ሲጓጓዙ ጉዳት እንዳይደርስባቸው አስፈላጊው ጥንቃቄ መደረጉንም አቶ አሕመድ ተናግረዋል።

ችግኞች በሚተከሉበት ወቅት አስፈላጊው ጥንቃቄ ይደረጋል ያሉት አቶ አሕመድ ለሥራው የሚያግዙ ቁሳቁሶች መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል።

በዞኑ አብዛኞቹ አካባቢዎች ዝናብ መዝነቡ ለችግኝ ተከላው ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አቶ አሕመድ ለአሚኮ ተናግረዋል።

የቅደመ ዝግጅት ሥራውን በደሴ ዙሪያ ወረዳ 037 ቀበሌ ጠባሲት በሚባለው አካባቢ ተገኝተውም ተመልክተዋል።

ነገ ከሚተከሉት ከ48 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ውስጥ 670 ሺህ ያህሉ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬ ችግኞች መኾናቸውንም ተናግረዋል።

በተከላ መርሐ ግብሩ ላይ ከ970 ሺህ በላይ ሕዝብ ይሳተፋል ተብሎም ይጠበቃል።

በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ላይ ሁሉም የዞኑ ሕዝብ እንዲሳተፍም የዞኑ ግብርና መምሪያ ጥሪ አቅርቧል።

ዘጋቢ፦ አሊ ይመር

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ልዩ ድጋፍ የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መብትና ጥቅም ለማስከበር የምክር ቤት አባላት ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት ይጠበቅባቸዋል” አፈጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ
Next articleለሐምሌ 10/2015 ዓ.ም የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ ዝግጅት መጠናቀቁን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ገለጸ።