“ልዩ ድጋፍ የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መብትና ጥቅም ለማስከበር የምክር ቤት አባላት ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት ይጠበቅባቸዋል” አፈጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ

28

ባሕር ዳር: ሐምሌ 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች ፎረም አባላት

ልዩ ፍላጎት ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች አካቶ ትግበራን በመከታተል ረገድ በሚኖራቸው ኀላፊነትና ተግባራት ዙሪያ ለአባላቱ ሥልጠና እየተሰጠ ነው።

ሥልጠናው በሥርዓተ ፆታ፣በሕጻናት፣አካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን ጉዳዮች አካቶ ትግበራ እና የሴቶችን ጥቃት መከላከል ላይ ያተኮረ ነው።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ በስልጠናው የመክፈቻ ንግግር እንዳሉት ሥልጠናው የምክር ቤት አባላቱ በክትትልና ቁጥጥር ተግባር አስፈጻሚ ተቋማት ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካላት አካቶ ትግበራን በአግባቡ እንዲፈጽሙ የሚያስችል ነው ብለዋል።

አባላቱ በተሰጣቸው ሥልጣንና ተግባር ልክ የሚያደርጉት ክትትልና ቁጥጥር በዕውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲኾን ታላሚ ተደርጎ የተዘጋጀ ስልጠና ስለመኾኑም ነው የተናገሩት።

“ልዩ ድጋፍ የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መብትና ጥቅም ለማስከበር የምክር ቤት አባላት ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት ይጠበቅባቸዋል” ነው ያሉት አፈጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ።

በሀገር ላይ ሁሉም ዜጋ እኩል ተጠቃሚ መኾን አለበት ፣ለዚህም በኀላፊነት መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አካላት የሀገርን ሀብት ይጠቀሙ ሲባል ትልቁ ፋይዳ ለሀገር ነው የሚሉት አፈጉባዔዋ ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካላት መብቶቻቸውና ጥቅሞቻቸውን በማስከበር ለሀገራቸው የሚችሉትን እንዲያበረክቱ እድል መሥጠት ነው ብለዋል።

የሀገርን ሃብት እኩል ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚቻለው በሕጉ መሰረት፣በተሰጣቸው መብት ልክ ተጠቃሚ እንዲኾኑ እድሉን በመስጠት ለሀገር የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካላትን ጥቅም ማስጠበቅ፣ መብቶቻቸውንም ማስከበር በአንድ ተቋም ብቻ የሚረጋገጥ ባለመኾኑ ሁሉም አስፈጻሚ ተቋም አካቶ ትግበራ ገቢራዊ የሚኾንበት ሕግ፣መመሪያ ፣ዓዋጆችና ደንቦች አሉ የሚሉት አፈጉባዔዋ ለዚህም ተፈጻሚነት የምክር ቤት አባላት ትልቅ ድርሻ እንዳለባቸው ነው ያስታወሱት።

አስፈጻሚ አካላት በሚሠሩት የአካቶ ትግበራ ሥራ የሕግ ክፍተቶችም ካሉ እንዲታረሙ አቅጣጫዎችን መስጠት ከአባላቱ ይጠበቃል ነው ያሉት አፈጉባዔዋ።

ስልጠናው ለስኬት እንዲበቃ አባላቱ በንቃት መከታተልና ወስዶ የመተግበር ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዓላማችን ሪከርዳችንን መስበር ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleየአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብርን ስኬታማ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማጠናቀቁን የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።