
ባሕር ዳር: ሐምሌ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአቶ ግርማ የሺጥላ የ40 ቀን መታሰቢያ እና ሃውልት ምረቃ ፕሮግራም በሰሜን ሸዋ ዞን መሐል ሜዳ ከተማ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ቤተክርስቲያን ተከናውኗል።
የ40 ቀን መታሰቢያና የሃውልት ምረቃ ሥነ-ሥርአቱ፤ የሃይማኖት አባቶች፣ የመሐል ሜዳ ምርጫ ክልል ተወካይ አቶ ወንዶሰን አድማሴ፣ የዞንና የወረዳ የሥራ ኃላፊዎች፣ የአቶ ግርማ የሺጥላ ቤተሰቦች እንዲሁም የቅርብ ጓደኞቻቸውና ወገኖቻቸው በተገኙበት በጸሎት፣ በመዝሙር፣ በቅኔ እና በመንፈሳዊ መልዕክት በታጀበ መልኩ ተከናውኗል።
የመንዝ ጌራ ምድር ወረዳ ዋና አሥተዳደሪ አቶ ኃይሌ የሺጥላ (የአቶ ግርማ የሺጥላ ወንድም) በሀዘናችን አዝናችሁ ላፅናናችሁን፣ ላጠነከራችሁን፣ በዚህም የ40 ቀን መታሰቢያ ፕሮግራም ላይ ተገኝታችሁ ላሰባችሁ፣ ሃውልቱንም ላስመረቃችሁ ውድ ወገኖቻችን ታላቅ ክብርና ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል፡፡
የመንዝ ጌራ ምድር ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጣልባቸው በቀለ እንደገለፁት ለወንድማችን አቶ ግርማ የሺጥላ እና አብረው ለተሰው ወንድሞቻችን ቤተሰቦች ድጋፍ የሚሆን ከመሃል ሜዳ ከተማ አስተዳደር ጋር በጋራ በመሆን እያዘጋጀን እንገኛለን፣ ከዛም ባለፈ ወንድማችን እና ታታሪ መሪያችን ያስጀመረውን ሌጋሲ በማስቀጠል ረገድ ኃላፊነት በመውሰድ በቁርጠኝነት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡
የመሐል ሜዳ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ ችሮታው ሹመት እንደገለፁት አቶ ግርማ የሺጥላ እና እብረው የተሰው ወንድሞቻችንን ሕይዎት መመለስ ባንችልም፣ ለቤተሰቦቻቸው ድጋፍ በማድረግ እንድሁም አቶ ግርማ የሺጥላ ለህዝባቸው ካደረጉት ድንቅ ስራዎች በመነሳት ለማመስገንና ለመዘከር ይሆን ዘንድ በመሐል ሜዳ ከተማ የተለያዩ መታሰቢያ ቦታዎችን በመሥራትና በስማቸው በመሰየም ለትውልድ ለማስተላለፍ የመሐል ሜዳ ከተማ አሥተዳደር ዝግጅት ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ መረጃው የአማራ ብልጽግና ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!