በደብረ ማርቆስ ከተማ በ205 ሚሊዮን ብር ወጪ በባለሃብቶች የተገነባው ወተትና የወተት ተዋፅኦ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ምርት ማምረት ጀመረ።

63

ባሕር ዳር: ሐምሌ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ)በደብረ ማርቆስ ከተማ በሁለገብ ኢንዱስትሪ ፓርክ በውጭና በሀገር ዉስጥ ባለሃብቶች ተገንብቶ የተጠናቀቀው “ጋፕ” ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ወተትና የወተት ተዋፅኦ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ወደ ምርት ገብቷል።

ፋብሪካው ” ጃና ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ፓስቸራይዝድ ወተትና የወተት ተዋፅኦ የሙከራ ምርት ማምረት ሂደትን አልፎ የማምረት ሥራውን በይፋ መጀመሩን የፋብሪካው ዋና ሥራ አሥኪያጅ ስለሽ ጌታነህ ተናግረዋል።

አቶ ስለሽ በወተት ልማት ለተሰማሩ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ትልቅ የገበያ ትስስር ይዞ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ ጥራቱን የጠበቀ የወተት ምርት በሰፊው ለገበያ ለማቅረብ እንደሚሠሩም አስረድተዋል፡፡

የወተት አቅርቦትን በመጨመር ጥራቱን የጠበቀ ምርት በወቅቱ በማቅረብ ከፋብሪካው ጋር በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መኾናቸውን የተናገሩት በወተት ልማት እና ግብይት የተሰማሩ የኅብረት ሥራ ማኅበራት አርሶ አደሮች ናቸው።

የፋብሪካው ወደ ሥራ መግባት ጥራቱን የጠበቀ ወተት በአጭር ጊዜ አሰባስቦ ለማስረከብ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል።

የወተት ተዋፅኦ ማቀነባበሪያ ፋብሪካው በዓይነቱ ዘመናዊና በምርት ጥራትና አመራረት ሂደት የሚኖረው አስተዋጽኦ የጎላ ነው ያሉት የፋብሪካው ፕሮዳክሽን ማናጀር ነገሰ ዘላለም ናቸው። ወተትና የወተት ተዋፅኦን አቀናብሮ በማሸግ ለተጠቃሚዎች እንደሚያቀርብም ነው ያስገነዘቡት። ፋብሪካው አሁን ላይ በቀን እስከ 30ሺህ ሊትር ወተት የማቀነባበር አቅም አለው ብለዋል።

በምርት ማስጀመር መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የደብረ ማርቆስ ከተማ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ትዕግስት የኔአባት በጎጃም እና አካባቢው ያለውን ሰፊ የወተት ሃብት ሳይባክን ለፋብሪካው በማቅረብ እና በማቀነባበር ጥራት ያለው ወተት ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ፋብሪካው ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በከተማው በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ሌሎች አልሚዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ እና የሥራ እድል እንዲፈጥሩ መምሪያው ድጋፍና ክትትል እያደረገ መኾኑን አስገንዝበዋል።

በ205 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገንብቶ ወደ ሥራ የገባዉ የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ግንባታው በ2010 ዓ.ም የተጀመረ ነው። አሁን ላይ ለ76 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩ ተገልጿል።

ዘጋቢ፦ ወንድወሰን ዋለ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለአርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) የክብር ዶክትሬት ሊሰጣት ነው።
Next articleየአቶ ግርማ የሺጥላ የሃውልት ምረቃ ፕሮግራም ተካሔደ።