ኢትዮጵያ በታችኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉዳት ላለማድረስ ቃሏን እንደምትጠብቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ ።

46

ባሕር ዳር: ሐምሌ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አደራ እና ቃልን ጠብቆ መገኘት የኢትዮጵያውያን መለያ እና መገለጫ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እነዚህ መገለጫዎች ከኢትዮጵያውያን ባህል እና እሴቶች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ መሠረት አንዱ እና ዋነኛው ቃልን ጠብቆ መገኘት እንደሆነም ጠቁመዋል።

ከዚህ በመነሣት ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን በምትገነባበት ወቅት በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ጉዳት ላለማድረስ ቃሏን ትጠብቃለች ብለዋል።

“ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ ከፈጣሪ ተችራለች፤ የዓባይ ወንዝ ፈጣሪ ለኢትዮጵያውያን የሰጠው አደራም ጭምር ነው፤ ሀገራችንም ይህንን አደራ ጠብቃ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ትጠቀማለች” ሲሉ አረጋግጠዋል።

ይህ እና የፈጣሪ ስጦታ የሆነው ታላቅ ወንዝ የላይኛው እና የተችኛው ተፋሰስ ሀገራትን አስተሳስሮ ለብዙ ሺህ ዓመታት የቆየ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ወንዙ ለእነዚህ ሀገራት የደም ስር በመሆኑ የሀገራቱን የሕዝብ ግንኙነት ያጠናከረ ሆኖ መቆየቱን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የዓባይ ወንዝን ከጎረቤት ሀገራት ጋር የምትጠቀመው በመተማመን እና በአደራ በመጠበቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ አሁንም ከድሮው በበለጠ አደራ እና ቃላችንን በመጠበቅ የጋራ ተጠቃሚነታችንን እንደምንቀጥል እናረጋግጣለን ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አሁን ያለውን የትምህርት ቤቶች ነባራዊ ኹኔታ መቀየር ካልቻልን ተወዳዳሪ ሀገርና ትውልድ መፍጠር አንችልም” ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
Next articleየኢትዮጵያ አንደኛ ሊግን የተቀላቀለው ደምበጫ ከነማ አቀባበል እየተደረገለት ነው።