“አሁን ያለውን የትምህርት ቤቶች ነባራዊ ኹኔታ መቀየር ካልቻልን ተወዳዳሪ ሀገርና ትውልድ መፍጠር አንችልም” ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

54

ባሕር ዳር: ሐምሌ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ለማሻሻል የሕዝባዊ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር በአማራ ክልል ተካሄዷል። በመድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ባለፉት ዓመታት የትምህርት ሽፋንን ለማሳደግ በርካታ ርቀት የተሄደ ቢኾንም ጥራት ያለው ትምህርት ከመስጠት አንፃር ግን በርካታ ስብራቶች ነበሩ ብለዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ ስብራቶችን ለማስተካከል የተለያዩ የለውጥ ሥራዎችን እያከናወነ መኾኑን የገለጹት ፕሮፌሰር ብርሃኑ “አሁን ያለውን የትምህርት ቤቶች ነባራዊ ኹኔታ መቀየር ካልቻልን ተወዳዳሪ ሀገርና ትውልድ መፍጠር አንችልም” ብለዋል።

በትምህርት ቤቶች ላይ የሚስተዋለውን የጥራት ችግር በመንግሥት አቅም ብቻ ለመፍታት ከሶስት አስርት ዓመታት ያላነሰ ጊዜ ሊወስድ ይችላል ያሉት ሚኒስትሩ ይህንን ሰፊ ችግር በቅርብ ጊዜ መፍታት የሚቻለው ማኅበረሰቡን እና ልዩ ልዩ የትምህርት ባለድርሻ አካላትን ቀጥተኛ ተሳታፊ በማድረግ በንቅናቄ በመሥራት ነው ብለዋል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ትምህርት ቤቶችን ለቀጣይ ትውልድ ምቹ አድርጎ ለመሥራትና የተሻለ ሀገር ለማስረከብ ትምህርት ሚኒስቴር በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገልጸው የተሻሉ ትምህርት ቤቶችን መፍጠር የሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ ኀላፊነት መኾኑን አስገንዝበዋል።
መላ ኢትዮጵያዊያንም የነገዋ ኢትዮጵያ መሰረት የኾኑ ትምህርት ቤቶችን የመገንባት ንቅናቄን መቀላቀል እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደሴ መምህራን ኮሌጅ የቀድሞ ተማሪዎች ከሶስት አስርት ዓመታት ቆይታ በኋላ በእውቀት ቤታቸው ዳግም ለበጎ ተግባር ተሰባሰቡ።
Next articleኢትዮጵያ በታችኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉዳት ላለማድረስ ቃሏን እንደምትጠብቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ ።