
ባሕር ዳር: ሐምሌ 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የቀድሞ የደሴ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ተመራቂዎች በ1985 ዓ.ም ነበር ከደሴ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የተመረቁት። በመምህርነት ሙያ የተመረቁት የያኔዎቹ ተማሪዎች ላለፉት ዓመታት በተለያዩ የሙያ መስኮች ተሰማርተው ሀገራቸውን በማገልገል ላይ ሲሆኑ ከ30 ዓመታት በኋላ የተለያዩ ዓላማዎችን ይዘው የእውቀት ‘ሀሁ’ን በቆጠሩበት ደሴ መምህራን ኮሌጅ ቅጥር ግቢ ተሰባስበዋል።
ከቀድሞ ተመራቂ ተማሪዎች አንዱ የሆኑት ወይዘሮ ዘላለም ጌታቸው የመረዳጃ ማኅበር ማቋቋማቸውንና በተመሰረተው ማኅበር በተለያየ ችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ለመደገፍ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የተማሩበት እና ለትልቅ ደረጃ ያደረሳቸው ደሴ መምህራን ኮሌጅን ለማጠናከር የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በመስራት ኮሌጁ የሚያስፈልገውን የማስተማሪያ ግብዓቶች ከማሟላት ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ደሴ ከተማ በያኔ ወጣትነት ዕድሜያችን ፍቅርን ሰጥታ ያሳደገችንና ለቁምነገር ያበቃችን በመሆኗ ሁልጊዜም በልባችን ውስጥ ናት ያሉት የማኅበሩ ሰብሳቢ አቶ መስፍን ትጉ የአሁኑ ትውልድም እንደኛ መልካም ዓላማን በመያዝ ያስተማራቸውንና ለወግ ማዕረግ ያበቃቸውን ማኅበረሰብ ዳግም መለስ ብለው ሊመለከቱ ይገባል ብለዋል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የኮሌጁ መምህራን ተማሪዎቻቸው ለበጎ ተግባር በመሰባሰባቸው የተሰማቸው ደስታ ትልቅ እንደሆነ ተናግረዋል።
የቀድሞ ተመራቂ መምህራኑ ባዘጋጁት መርኃ ግብር ላይ ለቀድሞ መምህራኖቻቸውና ለጓደኞቻቸው እውቅና እና ሽልማት ያበረከቱ ሲሆን በኮሌጁ ቅጥር ግቢ የ1985 ተመራቂዎች በሚል በተሰጣቸው ቦታ ላይ ችግኝ ተክለዋል።
ዘጋቢ:–ሰልሀዲን ሰይድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!